20 በመቶው የዩክሬን መሬት በሩሲያ ጦር መያዙን ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ተናገሩ
በየዕለቱ 100 የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ጦር እየተገደሉ መሆኑን ዜለንስኪ መናገራቸውም ይታወሳል
ፕሬዝዳንቱ በሉግዘንበርግ ፓርላማ የበይነ መረብ ንግግር አድርገዋል
20 በመቶው የዩክሬን መሬት በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር መዋሉን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ተናገሩ፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመሩ ሶስት ወራት ያለፈው ሲሆን እስካሁን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ሀገራቸውን ለቀው ወጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜለንስኪ ሩሲያን ለመመከት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ድጋፎችን ለማግኘት በጥረት ላይ ሲሆኑ በዛሬው ዕለትም ከሉግዘንበርግ ፓርላማ ጋር በበይነ መረብ ንግግር አድርገዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጊዜ እንዳሉት 20 በመቶ የሚሆነው የዩክሬን ግዛት በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር እንደወደቀ ተናግረዋል፡፡
የሃገራቸው ወታደሮች በ1 ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ ከሩሲያ ጦር ጋር ለሀገራቸው እየተዋደቁ እንደሆነም ነው ዜሌንስኪ የገለጹት፡፡
1 ሺ 730 የዩክሬን ወታደሮች እጅ መስጠታቸውን የሩሲያ ጦር አስታወቀ
ዩክሬን በየቀኑ ከ60 እስከ 100 የሚደርሱ ወታደሮቿን እያጣች መሆኑን ፕሬዝዳንቱ መናገራቸው ይታወሳል። ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን የሞቱትን ዩክሬናውያን አጠቃላይ ቁጥር ከመናገር ግን ተቆጥበዋል።
በምስራቅ ዩክሬን ያለው ሁኔታ “በጣም አደገኛ ነው” ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ በየቀኑ ቁጥራቸው 500 የሚደርሱ ሰዎች እየቆሰሉ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኒውስ ማክስ ከተባለ የመገናኛ ብዙሃን ጋር በኪቭ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በዩክሬን ያለው አጠቃላይ ሁኔታ በተለይም በምስራቅ ዩክሬን በሚገኙት ሴቪየርዶኔስክ እና ለይስቻንስክ ከተሞች ያለው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው ብለዋል።
ሴቪየርዶኔትስክ እና ለይስቻንስክ ከተሞች በምስራቅ ዩክሬን ከፍተኛ ውጊያ ከሚደረግባቸው ስፍራዎች ውስጥ ዋነኞቹ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሰኞ ሴቪየርዶኔስክ ከተማ ዙሪያ ላይ የነበረው የሩሲያ ጦር ወደ ከተማዋ ዘልቆ በመግባት መቆጣጠር መጀመሩ ይታወሳል።
እንደ አሜሪካ የደህንነት ተቋማት መረጃ ከሆነ በጦርነቱ እስካሁን ከ5500 እስከ 11 ሺህ የሚደርሱ የዩክሬን ወታደሮች ሞተዋል።