ዩክሬን በየቀኑ እስከ 100 የሚደርሱ ወታደሮቿን እያጣች መሆኑን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አስታወቁ
በምስራቅ ዩክሬን ሩሲያ ጥቃት ማጠናከሯን ተከትሎ ያለው ሁኔታ አደገኛ መሆኑን ፕሬዝዳትት ዘለንስኪ ገለጹ
በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት እስካሁን እስከ 11 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ
ዩክሬን በየቀኑ ከ60 እስከ 100 የሚደርሱ ወታደሮቿን እያጣች መሆኑን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ አስታወቁ።
በምስራቅ ዩክሬን ያለው ሁኔታ “በጣም አደገኛ ነው” ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ በየቀኑ ቁጥራቸው 500 የሚደርሱ ሰዎች እቆሰሉ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ኒውስ ማክስ ከተባለ የመገናኛ ብዙሃን ጋር በኪቭ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በዩክሬን ያለው አጠቃላይ ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው ብለዋል።
በተለይም በምስራቅ ዩክሬን በሚገኙት ሴቪየርዶኔትስክ እና ለይስቻንስክ ከተሞች ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሴቪየርዶኔትስክ እና ለይስቻንስክ ከተሞች በምስራቅ ዩክሬን ከፍተኛ ውጊያ ከሚደረግባቸው ስፍራዎች ውስጥ ዋነኞቹ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሰኞ ሴቪየርዶኔትስክ ከተማ ዙሪያ ላይ የነበረው የሩሲያ ጦር ወደ ከተማዋ ዘልቆ በመግት መቆጣጠር መጀመሩ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ከፍተኛ የተባለው ውጊያ በምስራቅ ዩክሬን እየተካሄደ መሆኑን በማከል፤ ጦራቸው በምስራቅ ዩክሬን በምትገኘው ከሃርኪቭ ከተማ ስኬታማ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በጦርነቱ ምክንያት በየቀኑ እስከ 100 የሚደርሱ ወታደሮቻው እየመቱ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፤ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን የሞቱትን ቁጥር ከመናገር ተቆጥበዋል።
የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት ባወጡት መረጃ ከሆነ የሩሲያ ዩክረን ጦርነት ከተጀመ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከ5 ሺህ 500 እስከ 11 ሺህ የሚደርሱ ዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ጠቁመዋል።
የተባባሩት መንግስታት ያወጣው መረጃ ደግሞ ጦርነቱ ከተጀመ ጊዜ አንስቶ በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች መሞታቸውን አስታውቋል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ሶስት ወራት አልፎታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት የዩክሬን ዋና ዋና የሚባሉ ከተሞችን ጨምሮ የንግድ ማሳለጫ ወደቦች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መውደማቸውም ይታወቃል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሜር ዘሌንስኪ ከቀናት በፊት ባሰሙት ንግግር፤ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው "ትርጉም-አልባ ጦርነት" እንዲያበቃ ምእራባውያን ከሩሲያ ጋር የገቡትን አላስፈላጊ ጨዋታ ሊያቆሙ ይገባል ብለዋል።