ቦርዱ ምርጫውን ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችል የቁሳቁስ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጿል
50 ሚሊዬን ኢትዮጵያውያን ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቦርዱ አስታወቀ
በመጪው ሃገራዊ ምርጫ 50 ሚሊዬን ኢትዮጵያውያን ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ቦርዱ ምርጫውን በማስመልከት እያደረገ ያለውን ዝግጅት ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል፡፡
50 ሺ 900 የምርጫ ጣቢያዎች ይኖራሉ ያለው ቦርዱ 50 ሚሊዬን ኢትዮጵያውያን ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።
ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ዝግጅትን ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ሊስተካከል በሚችል መልኩ አዘጋጅተናል ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እውነተኛነቱና ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቁሳቁሶቹ ሊያበላሻቸው በሚፈልግ የትኛውም አካል እንዳይበላሹ ሆነው መዘጋጀታቸውንም ነው ሰብሳቢዋ የገለጹት፡፡
ለማጭበርበር ወይም ሌላ ነገር ለማድረግ የማይመቹ ሆነው ተዘጋጅተዋልም ብለዋል፡፡
ከአሁን ቀደም በቦርዱ ማተሚያ ቤት ይታተሙ የነበሩት የመራጮች መመዝገቢያ ወረቀቶች በከፍተኛ ጥንቃቄ በውጭ ሃገር ታትመው ወደ ሃገር እንዲገቡ ተደርጓል እንደ ወ/ሪት ብርቱካን ገለጻ፡፡
ወረቀቶቹ በዱባይ መታተማቸው ከአሁን ቀደም መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
የተደረገው ዝግጅት ከአሁን ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች በምን እንደሚለይና የቁሳቁስ ዝግጅቱ ምን እንደሚመስልም ለጋዜጠኞች ገለጻ ያደረጉት የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ የምርጫውን ደህንነትና ተዓማኒነት ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
አማካሪዋ የመመዝገቢያ ቅጾቹ አንድ የምርጫ መዝገብ ሊይዛቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተካተውባቸው በልዩ የቁጥር ቅደም ተከተል በተሻለ ጥራት ተዘጋጅተዋል ያሉ ሲሆን የምርጫ ጣቢያዎች ከአሁን ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ አዲስ መለያ ቁጥር እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ድምጽ እንደሚሰጡ የሚጠበቁትን ኢትዮጵያውያን ለመመዝገብ የሚያስችሉ ሆነው በ5 የተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁት ጥራዞች 50 ሺ 900 ነው፡፡
ለማባዛትም ሆነ አመሳስሎ ለማተም በማያስችል መልኩ ልዩ ቁጥር እና ቀሪ እንዲኖራቸው ሆነው የተዘጋጁት የመራጮች መታወቂያ ካርዶችም 305 ሺ 400 ናቸው፡፡
በድምሩ 407 ሺ 200 ሰዎች ምዝገባውንና ምርጫውን ያስፈጽማሉም ተብሏል፡፡
የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት የሚከናወነው የመራጮች ምዝገባ ከተከናወነ በኋላ ነው፡፡
መራጮች በድምጽ መስጫው ቀን ደህንነታቸው በተጠበቀበት ነጻ ሁኔታ ድምጻቸውን ለመስጠት እንዲችሉ በልዩ መልኩ መከለያዎች ተዘጋጅተዋል ያሉት አማካሪዋ የምርጫ ህጉ በሚያዘው መልኩ ብርሃን በሌለበት ድምጽ ለመቁጠር የሚያስችሉ ከ101 ሺ በላይ የጠረጴዛ ባትሪዎች እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡
ድምጻቸውን በወረቀት ከሚሰጡት መራጮች ጋር ባይገናኝም የምርጫ ጣቢያዎችን የጂፒኤስ ኮኦርዲኔት ሊያመለክቱ የሚችሉ ከ50 ሺ በላይ ታብሌቶች ስለመዘጋጀታቸውም በጉብኝቱ ተገልጿል፡፡