በትግራይ ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ መንግስት ሊቋቋም ይችላል ተባለ
የትግራይ ክልል በፌዴራሉ መንግሥት እርምጃ ሊያስወስድ የሚችል ሕገ-መንግሥታዊ ጥሰት ስለመፈጸሙ አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል
በክልሉ አስተዳደር ላይ የኃይል እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔ ገልጸዋል
በትግራይ ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ መንግስት ሊቋቋም ይችላል ተባለ
የትግራይ ክልል በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ሕገ-መንግስቱን አደጋ ላይ መጣሉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አስታወቁ፡፡ አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ-መንግስታዊ ሂደቱን በጠበቀ መልኩ ምርጫውን እንዲራዘም ቢወስንም “ለሕገ መንግስቱ ተገዥ ያልሆኑና ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች ሕዝቡን የማወናበድ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡ ምርጫ ማስፈጸም የምርጫ ቦርድ ስራ ሆኖ የትግራይ ክልል ግን ኢ- ሕገ-መንግስታዊ በሆነ መልኩ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም፣ አግላይ በሆነ መንገድ ምርጫ በማካሄዱ በክልሉ አስተዳደር ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል በቂ ሕገ-መንግስታዊ መሰረት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ አደም የክልሉን ሕግ አውጪና ሕግ አስፈጻሚዎችን ማገድ እና ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ መንግስት ማቋቋምና የፌዴራል የፀጥታ አካላት በማሰማራት ሕገ-መንግስቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት መቆጣጠር ሊወሰዱ ከሚችሉ እርምጃዎች መካከል ናቸው፡፡
ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች መደበኛ ስራቸውን እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጉም በማሰጠት 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲራዘም ወስኖ ምርጫው እስኪካሔድ የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እና ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚተረጎም የሕገ-መንግሥት አንቀጽ አለመኖሩን በመጥቀስ የምርጫውን መራዘም የተቃወመው የትግራይ ክልል መንግሥት በክልል ደረጃ የምርጫ ኮሚሽን አቋቁሞ በክልሉ ምርጫውን አካሒዶ አዲስ መንግሥት መስርቷል፡፡
በትግራይ ምርጫው ከመካሔዱ በፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ክልሉ ምርጫውን ከማድረግ እንዲቆጠብ አሳስቦ ፌዴሬሽኑ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ያለው ምርጫው ቢካሔድ እንኳን በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 9 (1) መሰረት እንዳልተካሔደ ይቆጠራል በሚል ለምርጫው እውቅና እንደማይሰጥ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኮሮና ቫይረስ ስጋት አለመሆኑ ከታወቀ በኋላ ምርጫው እንዲካሔድ በሚወሰንበት ጊዜ የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫውን አልቀበልም የሚል ከሆነ ችግር እንደሚፈጠር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጤና ሚኒስቴር የቀረበለትን ምክረ-ሀሳብ ተቀብሎ ለምርጫው ዝግጅት እንዲደረግ ዉሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ምርጫው በትግራይ ክልልም ጭምር እንደሚካሔድ የም/ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የገለጹ ሲሆን ትግራይን የሚመራው ህወሓት ደግሞ የክልል ም/ቤት ምርጫ ከዚህ በኋላ የሚካሔደው ከ5 ዓመት በኋላ ነው ከማለቱም ባለፈ በባለስልጣናቱ አማካኝነት ለፌዴራሉ መንግስት ከመስከረም 25 በኋላ እውቅና እንደማይሰጥ ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፌዴራሉ መንግስት እና የትግራይ ክልል መንግስት ዉጥረት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የሕገ-መንግሥቱን ጥሰት ጨምሮ በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ የተለያዩ የጸጥታ ችግሮች አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ በማድረግ ይወነጃጀላሉ፡፡