መንግስት ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ 538 ተሽከርካሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ይዘው ግብተዋል ተባለ
ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ድጋፎችን ጭነው ከገቡ ተሽከርካሪዎች መካከል 72 በመቶ ያህሉ እስካሁን አልተመለሱም ተብሏል
በክልሉ ረሀብ ተከስቷል መባሉ ትክክል አለመሆኑንም የሰላም ሚኒስቴር ገልጿል
መንግስት ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ 538 ተሽከርካሪዎች የሰብዓዊ መብት ድጋፍ ይዘው ወደ ክልሉ መግባታቸውን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ዛሬ በሰጡት መግለጫ የፌደራል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ከመውጣቱ በፊት በትግራይ ክልል ለ4. 9 ሚሊዮን ዜጎች ለአንድ ወር የሚሆን የሰብዓዊ ድጋፍ አስቀምጦ ወጥቷል ብለዋል።
ሚኒስትሯ ከሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ 538 ተሽከርካሪዎች የሰብአዊ መብት ድጋፎችን ማድረሳቸውንም ገልጸዋል።
- የሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ “ከ100 በላይ የጭነት መኪኖች” መቀሌ ደረሱ
- በትግራይ ከ1 ሚሊዬን ለሚልቁ ተጨማሪ ሰዎች ምግብ ለማቅረብ መቻሉን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ
ይሁንና ወደ ክልሉ ከተሰማሩ ተሽከርካሪዎች መካከል 72 በመቶ ያህሉ እርዳታዎቹን ካደረሱ በኋለ እስካሁን አለመመለሳቸውን ሚኒስትሯ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት 14 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ ነክ እና 4000 ሜትሪክ ቶን የምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ተጓጉዘዋል።
እስካሁን ድረስ ከምግብ እና የምግብ ዕቃዎች በተጨማሪ የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ አካል የተለያዩ 30 የሚደርሱ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች በሳምንት 2 ጊዜ ከቦሌ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል በሚደረገው በአየር ትራንስፖርት 101 ሚሊዮን ብር ማጓጓዝ ችለዋልም ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሀት ቡድን የፌደራል መንግስት የትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ እንዲኖረው በሚል የተናጠል ተኩስ አቁሞ ከክልሉ ቢወጣም የህወሀት ቡድን ግን ወደ አማራ ክልል እና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱ ተገልጿል።
በዚህ ጥቃት ሳቢያ ለትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ድጋፎች ለሚፈልጉ ዜጎቻችን እርዳታዎችን በቀላሉ ማድረስ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
ይሁንና በክልሉ ረሀብ ተከስቶ የዜጎች ሀይወት እያለፈ ነው በሚል የሚቀርቡ ክሶች መሰረተ የሌላቸው ህዝቡ አሁንም ለህወሀት ሀይሎች ገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎችን በመለገስ ላይ መሆኑ ክሱን ውድቅ ያደርገዋል ሲሉም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በአፋር ክልል በኩል አሁንም ለተረጅዎች ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆናቸውን ወይዘሮ ሙፈሪያት አክለዋል።
ህወሀት ወደ አጎራባች ክልሎች በከፈተው ጥቃት ምክንያት ከ500 ሺህ በለይ ዜጎች ከትውልድ ቀዬዓቸው ሲፈናቀሉ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ለጉዳት መጋለጣቸው በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል።
የፌደራል መንግስት “ፖለቲካን እና ሰብዓዊነትን ለያይቶ ነው የሚያየው” ያሉት ሚኒስትሯ “ህወሀት በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት ማለትም ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በፊት በትግራይ ክልል 1.8 ሚሊዮን ዜጎች በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ ነበሩም ብለዋል።
በጦርነቱ ምክንያትም በክልሉ የተረጅዎች ቁጥር ወደ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ማሻቀቡን ገልጸው ለነዚህ ሁሉ የሰብዓዊ እርዳታዎች በመድረስ ላይ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በሰብአዊ መብት ድጋፍ ስም ለህወሀት ያልተፈቀዱ ድጋፎችን ለማድረስ ሲሞክሩ የተያዙ የረድዔት ተቋማት መገኘታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት የተቋማቱን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበው የማስተካከያ እርምጃ በመወሰድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።