ዩክሬን በጦርነቱ 113 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ወድሞባታል ተብሏል
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ከሉዓላዊ ግዛቷ 20 በመቶ የሚሆነውን ማጣቷ ተገልጿል።
በጦርነቱ ዩክሬን 20 በመቶ ግዛቷ በሩሲያ መወሰዱን ኒውዮርክ ታይምስ የዘገበ ሲሆን፤ በጦርነቱ ሳቢያ የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩም ተገልጿል።
ዩክሬን ካጣቻቸው ግዛቶቿ መካከል የዶኔስክ እና የሉሃንስ ግዛቶች ተጠቃሾች ሲሆን፤ ሩሲያ ግዛቶቹን ነጻ ሀገራት ናቸው የሚል ዕውቅና መስጠቷ ይታወሳል። ከዚህ ባለፈም ሩሲያ በግዛቶቹ ፓስፖርት መስጠቷም ይታወሳል።
በጦርነቱ እስካሁን 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ስደተኛ መሆናቸውንም ነው የዓለም መገናኛ ብዙኃን የዘገቡት።
ስድስት ወራትን ባስቆጠረው በዚህ ውጊያ የደረሰው ሰብዓዊ ቀውስና የፋይናንስ መጠን ከሚታሰበውና ከሚገመተው በላይ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ከመጋቢት 24 ቀን 2022 ጀምሮ በተደረገው በዚህ ውጊያ 5 ሺ 587 የዩክሬን ዜጎች ህይወታቸው አልፍል ተብሏል። ምንም እንኳን የሟች ንጹሃን ቁጥር ከ 5 ሺ በላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ትክክለኛ ቁጥሩ ግን ከዚህም ሊልቅ ይችላል ተብሏል።
ኒውዮርክ ታይምስ የስድስት ወራቱን ውጊያ በተመለከተ ባዘጋጀው ጹሑፍ ከዩክሬን ወታደሮች ይልቅ ብዙ የሩሲያ ወታደሮች መሞታቸውን ገልጿል።
ጄነራል ቫልሪ ዛሉዚኒ የተባሉ የዩክሬን ጦር መሪ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ እስካሁን 9 ሺ ወታደሮች እንደተገደሉባቸው ጠቅሰዋል። ይሁንና ይህ ቁጥር በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም ተብሏል። 25 ሺ የሩሲያ ወታደሮች መገደላቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ቢገልጽም ቁጥሩን ከየትኛው ምንጭ እንዳገኘው አልጠቀሰም።
ዩክሬን በዚህ ጦርነት የግዛቷን 20 በመቶ ማጣቷን የተገለጸ ሲሆን ከዩክሬን በኩል 113 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ወድሟል ተብሏል።
ኪቭ በጦርነቱ ያጣችውን ሁሉን አቀፍ ጉዳትና ውድመት ለመመለስ 200 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል ተብሏል።
የዩክሬን አጋሮች እስካሁን 83 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል መግባታቸው የተገለጸ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት የግብርና ምርቶች ለዓለም መድረስ አለመቻላቸው ይታወቃል።