ከ10 ኢትዮጵያዊያን ስድስቱ በድህነት ውስጥ ይኖራሉ - ጥናት
ኑሯቸው ጥሩ ነው ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር 38 በመቶ ብቻ እንደሆኑ አፍሮ ባሮ ሜትር የተሰኘው የጥናት ተቋም ይፋ አድርጓል
ጥናቱ 68 በመቶ ኢትዮጵያዊያን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ "መጥፎ" ደረጃ ላይ መድረሱን እንደሚያምኑም አመላክቷል
ከ10 ኢትዮጵያዊያን ስድስቱ በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ አዲስ ጥናት አመላከተ።
አፍሮ ባሮ ሜትር የተሰኘው የጥናት እና ማማከር አገልግሎት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ያስጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል።
በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች እንደተጠና የተገለጸው ይህ ጥናት 2 ሺህ 400 ሰዎች ተሳትፈዋል ተብሏል።
ጥናቱ በ300 የጥናት መቁጠሪያ ማዕከላት እና 26 የጥናት ጣቢያዎች በፈረንጆቹ 2023 ዓመት እንደተካሄደ በተገለጸው በዚህ ጥናት መሰረት 68 በመቶዎቹ ተሳታፊዎች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ "መጥፎ" ደረጃ እንደሚገኝ ያምናሉ ተብሏል።
እድሜያቸው ከ18-55 የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በገጠር እና ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በጥናቱ እንደተሳተፉም ተገልጻል።
እንዲሁም በጥናቱ ከተሳተፉ ሰዎች ውስጥ 51 በመቶዎቹ ወንድ 49 በመቶዎቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው ከዚህ በተጨማሪም 66 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች የገጠር ነዋሪዎች ናቸውም ተብላል።
በጥናት ማዕከሉ ብሔራዊ አጥኒ የሆኑት አቶ ሙሉ ተካ ፤ አፍሮ ባሮ ሜትር የጥናት ማዕከል በተለያዩ ጉዳዮች በሁለት ዓመት ተኩል አንዴ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያስጠናቸውን ጥናቶች ይፋ ያደርጋል ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት በተደሩገው ጥናት መሰረትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ "መጥፎ" ወይም "በጣም መጥፎ" ነው ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በ2020 ከነበረበት 44 በመቶ ወደ 65 በመቶ ከፍ ማለቱም በጥናት ሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
በጥናቱ ከተሳተፉ ሰዎች ውስጥም 42 በመቶዎቹ በቀጣዮቹ 12 ወራት ውስጥ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለው ያምናሉ የተባለ ሲሆን 38 በመቶዎቹ ደግሞ የኢኮኖሚ ቀውሱ ቢብስበት እንጂ አይሻሻልም ብለው እንደሚያምኑ ተገልጿል።
በጥናቱ ሪፖርት መሰረት በየ ዕለቱ ወይም ሁልጊዜ ገቢ የሚያገኙ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር 37 በመቶ ያህል ነው።
እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ከ10 ኢትዮጵያዊያን ስድስቱ በድህነት ኖረዋል የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 34 በመቶዎቹ በአስከፊ ድህነት የሚኖሩ ናቸናቸው ሲል የጥናቱ ሪፖርት ያስረዳል።
በኢትዮጵያ አሁንም የሚታረስ መሬት መኖሩ እንዲሁም የጸጥታው ሁኔታ ከተሻሻለ ኢኮኖሚው ሊሻሻል እንደሚችል በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል።
አፍሮ ባሮ ሜትር ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶችን ይፋ የሚያደርግ ፓን አፍሪካ ተቋም ነው።