70 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ነው
በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን የመመለስ ስራ በ2 ሳምንት ውስጥ ይጀመራል ተብሏል
መንግስት ከዚህ ቀደም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሃገር መመለሱ ይታወቃል
በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮያውያንን ወደ ሀገራቸው ሊመልስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ “በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 70 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው የመመለስ ሦስተኛ ምዕራፍ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይጀምራል” ብለዋል።
በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮያውያንን ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ መክሯል።
የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሥራ በብሔራዊ ኮሚቴው ውስጥ የታቀፉት የፌዴራል ተቋማት እና የክልሎችን የጋራ ቅንጅት ይጠይቃል ብለዋል።
ከወዲሁ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተሟላ ሁኔታ በፍጥነት መጠናቀቅ እንደሚገባቸውም አምባሳደር ብርቱካን ተናግረዋል።
አምባሳደር ብርቱካን ዜጎችን የማስመለሱ ሥራ የተሳካ እንዲሆን ከወዲሁ አስፈላጊው በጀት፣ የሎጀስቲክ እና አዲስ አበባ ሲደርሱ ወደየ መነሻቸው እስከሚጓዙ ድረስ የሚቆዩባቸው መጠለያዎች ዝግጁ እንዲደረጉ ለባለድርሻ አካላት አስገንዝበዋል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ክልሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ዕቅዱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጠዋል።
መንግስት ከዚህ ቀደም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሃገር መመለሱ ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም ከ2009 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት 3 ዓመታት ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል።