አዲስ አበባን ጨምሮ በ3 ክልሎች መራጮች ከተገመተው በላይ ካርድ ወስደዋል ተባለ
ምርጫ ቦርድ በመራጮች ምዝገባ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየመከረ ነው
እስከ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በአጠቃላይ 36.2 ሚሊዬን መራጮች ካርድ መውሰዳቸው ተነግሯል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያ በአዲስ አበባ በመወያየት ላይ ናቸው።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ ትናንት የተጠናቀቀውን የመራጮች ምዝገባ እንቅስቃሴ በተመለከተ ንግግር አድርገዋል፡፡
ምዝገባው እንዴት እንደነበር፣ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ካሉ እና ሌሎች ከምርጫው ጋር የተያያዙ ስራዎች በዛሬው ውይይት ላይ እንደሚገመገሙም ነው ሰብሳቢዋ የተናገሩት።
በቀጣይ የሚከናወኑ የምርጫ ስራዎችም በዚህ መድረክ ላይ ከፓርቲዎቹ ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሏል።
የመራጮች ምዝገባው ትናንት ተጠናቋል፡፡
እስከ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ያሉ የቦርዱ መረጃዎች በአጠቃላይ 36 ሚሊዮን 245 ሺህ 444 ሰዎች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን አመልክተዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 16.6 ሚሊዮኑ ሴት 19.5 ሚሊዮኑ ወንድ ናቸው፡፡
50 ሚሊዬን ዜጎች ካርድ ሊወስዱ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር፡፡ አሁን ያለው ካርድ የወሰዱ ዜጎች ቁጥሩ የግምቱን 78 በመቶ ይሸፍናል።
ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ከተገመተው በላይ የመራጮች ካርድ የተወሰደባቸው ክልሎች ናቸው።
በአዲስ አበባ ከ1.4 ሚሊዬን፣ በአፋር ከ1.7 ሚሊዬን፣ በአማራ ከ5.9 ሚሊዬን፣በቤንሻንጉል ከ174 ሺ፣ በጋምቤላ ከ326 ሺ፣ በኦሮሚያ ከ15.9 ሚሊዬን፣በሃረር ከ135 ሺ፣በድሬዳዋ ከ177 ሺ፣ በደቡብ ብ/ብ/ህ ከ4.8 ሚሊዬን፣ በሲዳማ ከ1.5 ሚሊዬን እና በሶማሌ ከ3.9 ሚሊዬን በላይ መራጮች ካርድ መውሰዳቸውን የቦርዱ የመረጃ ሰንጠረዥ ያመለክታል፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የመራጮች ምዝገባ የተከናወነበት ክልል ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ብዙ መራጮች ተመዝግቧል።