“70 በመቶ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ይገኛሉ”- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
የአውሮፕላን በረራዎች ዳግም መፈቀዳቸውን አምባሳደር ሬደዋን አስታውቀዋል
35 የምግብ የጫኑ እና 3 መድሃትና የህክምና ቁሳቁሰ የያዙ መኪናዎች ሽሬ ደርሰዋል
70 በመቶ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መሆናቸውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የነበረው የድርድር ውጤት በሳለፍነው ጥቅምት 23 ምሽት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በድርድሩ ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች ውስጥም ግጭትን በዘላቂነት ማቆም፣ ሰብዓዊ እርዳታን ያለገደብ ማድረስ፣ በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ህግና ስርዓትን ማስከበር አንዲሁም የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታትየሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያን መንግስት በመወከል በደቡብ አፍሪካው ድርድር ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው፤ እርዳታን በተመለከተ ምንም አይነት እንቅፋት እንደሌላ አስታውቀዋል።
“70 በመቶ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ይገኛሉ” ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ ከዚህ ከቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የሰብዓዊ እርዳታዎች በስፋት እየደረሱ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።
የሰብዓዊ እርዳታዎች መከላከያ በልያዛቸው አካባቢዎችም ጭምር እየደረሱ እንደሆነም ነው አምባሳደር ሬድዋን ያስታወቁት።
በተጨማሪም የሰባዓዊ ድጋ የአውሮፕላን በረራዎች መፈቀዳቸውን ያስታወቁት አምባሳደር ሬድዋን፤ መሰረታዊ አገልግሎቶችም ዳግም እየተጀመሩ እንደሆነም አስታውቀዋል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው ስምምነትም መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል እድል የሰጠ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ድርድር የተቋረጡ አገልግሎቶችን ማስጀመር ስምምነት ከተደረሰባቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።
ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ተቋርጦ ከነበረባቸው አካባዎች መካከል በተወሰኑት ዳግም የቴሌኮም አገልግሎት እንዳስጀመረ መግለጹ ይታወሳል።
አላማጣ፣ ኮረም እና ዓዲ አርቃይ የቴሌኮም አገልግሎት ከተጀመረባቸው አካባቢዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።