በ70 ዓመታቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ለመማር ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የገቡት አዛውንት
አዛውንቱ አቶ ዮሃንስ አዲሴ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና አልፈው ነው ወደ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡት
የ10 ልጆች አባትና የልጅ ልጆችን ማየት የቻሉት አቶ ዮሃንስ “ለመማር በቂ ዝግጅት አድርጌአለሁ” ብለዋል
የ70 ዓመት አዛውንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመማር ዩኒቨርሲቲን መግባቸው የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲን ዘንድሮ ከተቀላቀሉ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች መካከል የ70 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ ዮሃንስ አዲሴ ይገኛሉ።
የ70 ዓመት አዛውንት የሆኑት አቶ ዮሃንስ አዲሴ የ2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰውን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና አልፈው ወደ ተመደቡበት ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ መግባቸውንም ዩኒቨርሲቲው ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
የ10 ልጆች አባትና የልጅ ልጆችን ማየት የቻሉት አቶ ዮሃንስ በልጅነታቸው ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩና ባጋጠማቸው የአካል ጉዳት ምክንያት ለብዙ አመታት ከትምህርት ገበታ የራቁ ቢሆንም ለትምህርት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ያቋረጡትን ትምህርት እንደቀጠሉ ይናገራሉ።
በሀዲያ ዞን ዱና ወረዳ ለጠቦ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አዛውንቱ የ2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስደው ካለፉ ጥቂት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች አንዱ በመሆን ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል።
በ70 ዓመታቸው ዩኒቨርሲቲ የገቡት አቶ ዮሃንስ ከሀገሪቱ ክፍሎች ከሚመጡ ተማሪዎች ጋር ለመማር በቂ ዝግጅት አድርጌአለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዩኒቨርሲቲ ለተደረገላቸው ልዩ አቀባበል መደሰታቸውን ገልፀዋል።