በየመን 78 ሰዎች ተረጋግጠው ህይወታቸው አለፈ
እርዳታ ለመቀበል በተሰባሰቡ የመናውያን መካከል በተፈጠረው ግርግር በርካታ ሰዎች ቆስለዋል
አደጋው የመናውያን ላለፉት ስምንት አመታት ያሳለፉት የሰብአዊ ቀውስ ማሳያ ነው ተብሏል
በየመን እርዳታ ለመቀበል የተሰባሰቡ ዜጎች ተረጋግጠው በጥቂቱ የ78 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።
13 ሰዎችም እጅግ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው አልሚስራህ ቴሌቪዥንን ጠቅሶ ሬውተርስ የዘገብው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የመናውያን በአንድ ትምህርት ቤት በረመዳን ጾም ማብቂያ ከሁለት ባለሃብቶች የሚሰጥ ድጋፍን ለመቀበል ተሰሳስበው ነበር።
ድጋፉ 5 ሺህ የየመን ሪያል ወይም 9 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ነው የተባለ ሲሆን፥ ይህን ድጋፍ ለመውሰድ በተፈጠረ ግርግር በርካቶች ህይወታቸው አልፏል።
በሃውቲ ቴሌቪዥን የቴሌግራም ገጽ ላይ የተለጠፈው ተንቀሳቃሽ ምስልም የጸጥታ ሃይሎች እርዳታውን ለመውሰድ የሚጋፉ ሰዎችን ወደኋላ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ያሳያል።
ከመረጋገጥ አደጋው በኋላ ልብ የሚሰብሩ ምስሎች እየወጡ ነው፤ የወዳደቁ ጫማዎችና ልብሶች ሜዳ ላይ ወድቀው ይታያሉ።
ፖሊስም ልብሶቹን ለፎረንሲክ ምርመራ መሰብሰቡ የተነገረ ሲሆን፥ ለበዓል ድጋፍ ለመውሰድ የመጡ የመናውያን ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆነዋል የተባሉት ባለሃብቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
ስምንት አመት ያለፈው የየመን የእርስ በርስ ጦርነት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለረሃብ ዳርጓል።
ሳኡዲ በፈረንጆቹ 2015 ወደ ሰንአ ከገባች በኋላም የመን የኢራን እና ሳኡዲ አረቢያ የእጅ አዙር ጦርነት ሜዳ መሆኗ ይታወሳል።
ኢራን እና ሳኡዲ አረቢያ በቻይና አሸማጋይነት እርቅ ከፈጸሙ በኋላ ግን በየመን የሰላም አየር መንፈስ ስለመጀመሩ እየተነሳ ነው።
የሳኡዲ እና የሃውቲ መሪዎችም በሰንአ ምክክር ማድረጋቸው ትልቅ ተስፋን ፈጥሯል።
ዛሬ የተፈጠረው አደጋ ግን የመናውያን ባለፉት ስምንት አመታት በእጅ አዙር ፍልሚያው የደረሰባቸው ሰብአዊ ቀውስ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ እየተነሳ ነው።