የሃውቲ አማጺያን በየመን ተኩስ ለማቆም አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጡ
ቡድኑ የአማጺያኑ ደመወዝ በመንግስት በጀት እንዲከፈልና የሰንአ አውሮፕላን ማረፊያ እና የሁዴይዳ ወደብ ይከፈቱ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ነው ያስቀመጠው
ኦማን በመንግስታቱ ድርጅት አደራዳሪነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማረዘም ባለፈው ሳምንት ልኡኳን መላኳ ይታወሳል
ኦማን በየመን አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥረት እያደረገች ነው።
ሙስካት ባለፈው ሳምንት ወደ ሰንአ የላከችው የልኡክ ቡድንም ከሃውቲ አማጺያን ጋር ተነጋግሯል።
በመንግስታቱ ድርጅት አደራዳሪነት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተጠናቀቀ ሶስት ወራትን አስቆጥሯል።
ይህን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲጣስ የቆየ ስምምነት በአዲስ መልክ ለማራዘም ወደ ሰንአ ያቀኑት የኦማን የልኡካን ቡድን አባላት ከሃውቲ አማጺያን ያገኙት ምላሽ ግን ተስፋ አስቆራጭ ነው ተብሏል።
የሃውቲ አማጺያን አዲስ የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች አለም አቀፍ እውቅና በተሰጠው የየመን መንግስት ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ አይጠበቅም።
ሃውቲ የአማጺያኑ ደመወዝ በመንግስት በጀት እንዲከፈልና የሰንአ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም የሁዴይዳ ወደብ ያለምንም ቁጥጥር እንዲከፈቱ የሚል ቅድመ ሁኔታዎችን ነው ያስቀመጠው።
የቡድኑ ዋነኛ መሪ ጃላል አል ሩዋይሻን ፥ አማጺያኑ ደቡባዊ የመንን የሚያስተዳድሩ ህጋዊ መሪዎች መሆናቸው እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
የሰንአ አውሮፕላን ማረፊያ እና የሁዴይዳ ወደብም ተከፍተው ያለምንም ቁጥጥር የጦር መሳሪያዎችን ማስገባት እንዲችሉ መጠየቃቸውንም የቡድኑ ቴሌቪዥን አልሚስራህ ዘግቧል።
አማጺያኑ ከቴህራን እና ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያገኙ ይነገራል።
ቡድኑ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች የኦማን ጥረት የመሳካት እድሉ ጠባብ መሆኑን ያሳያል ነው የተባለው።
የየመን እውቅና ያለው መንግስት ባወጣው መግለጫም ቡድኑ የሰንአ አውሮፕላን ማረፊያ ዝግ እንደሆነና የሁዴይዳ ወደብም ምግብና ሌሎች ግብአቶች እየገባበት እንደማይገኝ መግለጹ ፍጹም ሀሰት ነው ብሏል።
አማጺያኑ የሰላም ስምምነት ላይ ላለመድረስ የሚጠቀሙት ማወናበጃ ነው ሲልም አጣጥሎታል።
የኦማንን ተደጋጋሚ ጥረት ያደነቀው መግለጫው ከሃውቲ ጋር የሚደረገው የሰላም ንግግር ቡድኑ ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምክንያት የመሳካት እድሉ ዝቅ ያለ መሆኑን ጠቁሟል።
ሳኡዲ አረቢያም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አሜሪካ ጋር በመሆን ባለፈው ወር በየመን አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥረት ማድረጓ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ከተጠናቀቀ ሶስት ወራትን ያስቆጠረው ተኩስ አቁም እስካሁን ሊታደስ አልቻለም።
ከ2014 ጀምሮ ሀገራት በእጅ አዙር የሚፋለሙባት የመን ሰላሟን ለመመለስም ሆነ ከ80 በመቶ በላይ የተራበ ዜጋዋን የሚመግብ ሁነኛ አጋር አላገኘችም።
በተኩስ አቁም ስምምነቱ ወቅት አቅሙን እያደረጁ ቆይተዋል የተባለላቸው የሃውቲ አማጺያንም ለአዲስ ጦርነት እየተዘጋጁ ስለመሆኑ ነው የተገለጸው።