የፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ጣልቃ ሊገባና እርምጃ ሊወስድ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
ትግራይ ክልል “በጀመረው እንቅስቃሴ የሚቀጥል ከሆነ እንቅስቃሴውን ለማስተካከል የሚያስችል ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ ይወሰዳል”-የፌዴሬሽን ምክር ቤት
ትግራይ ክልል “በጀመረው እንቅስቃሴ የሚቀጥል ከሆነ እንቅስቃሴውን ለማስተካከል የሚያስችል ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ ይወሰዳል”-የፌዴሬሽን ምክር ቤት
የፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ጣልቃ ሊገባና እርምጃ ሊወስድ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
በቅርቡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔነት የተሾሙት አቶ አደም ፋራህ የትግራይ ክልል ምክር ቤቱ ምርጫን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ ወደ ጎን በማለት የሚያደርገው እንቅስቃሴ “ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ ነው” ሲሉ ከኢቲቪ ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ህገ መንግስቱና ያሳለፈው ውሳኔ እንዲከበር በማሳሰብ ለጻፈው ደብዳቤ ምላሽ የሰጠው ክልሉ ግን የፈጸመው ምንም ዓይነት ህገ መንግስታዊ ጥሰት እንደሌለ ነው ያስታወቀው፡፡
አፈ ጉባዔው በበኩላቸው ክልሉ በጀመረው እንቅስቃሴ የሚቀጥል ከሆነ “ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ” እንደሚወሰድበት በዜናው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
“ህገመንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ካለ ወይም ከተፈጸመ” የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ሊገባ የሚችልባቸው ድንጋጌዎች እንዳሉም ነው የገለጹት፡፡
ለመሆኑ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ይገባል ሲባል ምን ማለት ነው? በምን ምክንያቶችስ ጣልቃ ይገባል? ገብቶስ ምን ያደርጋል? ይህን ለማስፈጸም በወጣው አዋጅ የተካተቱ ድንጋጌዎችስ ምን የሚሉ ናቸው?
የፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ጣልቃ ይገባል ሲባል?
የፌዴራል መንግስቱ ህገመንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ሊያስጠብቅ የሚችልበት ስልጣን ተሰጥቷል፡፡ ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ዐቅም በላይ ሆነ የጸጥታ መደፍረስ አልያም ሌሎች ችግሮች ሲያጋጥሙ ጣልቃ ሊገባና የተለያዩ እርምጃዎችን ሊወስድ የሚችልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉም በህገ መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ይህ ግን በክልል መስተዳድሮቹ ጥያቄ መሰረት አልያም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝ የሚሆን ነው፡፡
ሆኖም ሰብዓዊ መብቶች በሚጣሱበትና ክልሎቹ ለማስቆም በማይችሉበት ሁኔታ ያለ ክልሎቹ እውቅና ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ይህ ግን ሁለቱ ምክር ቤቶች በሚያደርጉት የጋራ ስብሰባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በራሱ ተነሳሽነት ጥያቄውን በማቅረብ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከተቻለ ብቻ የሚሆን ነው፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ መውደቁን ባረጋገጠ ጊዜ የፌዴራል መንግሰቱ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በህገ መንግስቱ አንቀጽ 62 (9) ላይ ተደንግጓል፡፡
እነዚህኑ ድንጋጌዎች ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችል የታመነበት አዋጅም በ1995 ዓ/ም ወጥቶ ተግባር ላይ ውሏል፡፡
ጣልቃ ሊገባና እርምጃ ሊወስድ የሚችልባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
‹‹የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ›› የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 ሕገመንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ ፌዴራል መንግስቱ እንዴት ባለ መንገድ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
በተለይም በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፣ የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ወይም ጥሰቱ እንዲቆም በአዋጁ መሰረት የተሰጠውን መመሪያ አለማክበር ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ተደርጎ እንደሚቆጠር መንግስት ጣልቃ ሊገባ ስለሚችልባቸው መሰረቶች በሚያትተው የአዋጁ አራተኛ ክፍል አንቀጽ 12 ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ጣልቃ ገብቶ ምን ያደርጋል?
የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ የሚገባው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲያዘው ነው፡፡ ምክር ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት ወይም ከተወካዮች ምክር ቤት ወይም ከሌላ ከማናቸውም አካል አንድ ክልል ህገ መንግስቱን በመጣስ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ እንደጣለ መረጃ ሲደርሰው አስፈላጊውን ማጣራት ካደረገ በኋላ የአደጋውን መኖር አለመኖር ለመወሰን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ሌላ መንግስታዊ አካል አጣርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብለት ለማዘዝ ይችላል፡፡
የቀረበለትን ሪፖርት ወዲያውኑ መርምሮ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ ያዛል፡፡
በትዕዛዙ መሰረት ጣልቃ የሚገባው የፌዴራል መንግስትም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለው ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
ምክር ቤቱ በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረትም መንግስት የፌዴራል ፖሊስን ወይም የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ወይም ሁለቱንም በክልሉ ሊያሰማራ፣የክልሉን ምክር ቤት እና ከፍተኛ የህግ አስፈጻሚ አካል በማገድ ለፌዴራል መንግስቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደርን ሊያቋቁምም ይችላል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለው ሁኔታ መወገዱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እስካመነበት ጊዜ ድረስ ወይም እስከ ሁለት ባሉት ዓመታት ውስጥ በክልሉ ሊቆይ እንደሚችልም በአዋጁ ተቀምጧል፡፡