በኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ለመመስረት ሕዝበ ውሳኔ ሊደረግ ነው
የደቡብ ክልል 5 ምዕራባዊ ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል ለመደራጀት በየምክር ቤታቸው ከሳምንት በፊት አጽድቀዋል
የፌዴሬሽን ም/ቤት የ”ደቡብ ምዕራብ ህዝቦች” ክልልን ለመመስረት ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ ወስኗል
በኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ለመመስረት ሕዝበ ውሳኔ ሊደረግ ነው
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው ስብሰባ በደቡብ ክልል ምዕራባዊ ክፍል የሚገኙ 5 ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል ለመደራጀት ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀበለ፡፡
በክልሉ የሚገኙት 5 ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ባለፈው ሳምንት በየምክር ቤቶቻቸው የጋራ ክልል ለመመስረት ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል፡፡
የምዕራብ ኦሞ፣ የሸካ፣ የከፋ፣ የዳውሮ፣የቤንች ሸኮ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው በደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልልነት እንዲደራጁ የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ተቀብለው በምክር ቤት ደረጃ ያጸደቁት፡፡
የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳው ምክር ቤቶች ከሳምንት በፊት መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔዱት መደበኛ ጉባዔ በ”ደቡብ ምዕራብ ህዝቦች” ክልልነት እንዲደራጁ ከአሁን ቀደም በመንግስት የቀረበውን ምክረ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል፡፡
ይህንን ውሳኔ የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳው ምክር ቤቶች ለደቡብ ክልል ም/ቤት አቅርበው ም/ቤቱ ደግሞ ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት የመራ ሲሆን በዚሁ ጉዳይ ዛሬ ውይይት ያደረገው የፌዴሬሽን ም/ቤት ጥያቄውን ተቀብሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ ወስኗል፡፡
በክልልነት ለመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ የደቡብ ክልል ዞኖች 13 ቢሆኑም ህጋዊውን መንገድ በተከተለ መንገድ ያልመጣለት በመሆኑ በሌሎቹ ጥያቄ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አለመወያየቱን እና ውሳኔ አለመስጠቱን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሌሎች ከአደረጃጀት ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልል የሚነሱ ጥያቄዎች በዚሁ ጉዳይ የተደረገውን ጥናት መሰረት በማድረግ እና ህጋዊነትን ተከትሎ በሂደት እንደሚታይም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ህዝቦችን ክልል ለመመስረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ይወሰን እንጂ ሕዝበ ውሳኔው መቼ ሊካሔድ እንደሚችል የተባለ ነገር የለም፡፡ ሕዝበ ውሳኔው ተደራጅቶ ክልሉ የሚመሰረት ከሆነ 11ኛ ክልል የሚሆን ሲሆን ከሲዳማ ቀጥሎ በኢትዮጽያ በሕዝበ ውሳኔ የሚደራጅ ሁለተኛው ክልል ይሆናል፡፡
ነባሩን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በማፍረስ ከሲዳማ ክልል ውጭ በሶስት ክልሎች እና በአንድ ልዩ ዞን ለማደራጀት ከአሁን ቀደም የቀረበው ምክረ ሃሳብ ምዕራብ፣ ማዕከላዊ፣ ኦሞቲክ ክልሎች እና ጌዴኦ “ልዩ ዞን”ን የሚያካትት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ/ም ከነባሩ ክልል የየደረጃው አመራሮች ጋር ከተወያዩ በኋላ ምክረ ሃሳቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ምክር ቤቱም የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ይዞ እንዲቀርብ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑም አይዘነጋም።