የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን የድጋፍ ቁሳቁሶች ይዞ ዛሬ ወደ ሱዳን ያቀናል
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የሚመሩት ልዑክ ድጋፉን ይዞ ዛሬ ከሰዓት ወደ ካርቱም ይጓዛል
በሱዳን የጎርፍ አዳጋ ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሀዝብ ተፈናቅሏል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን የድጋፍ ቁሳቁሶች ይዞ ዛሬ ወደ ሱዳን ያቀናል
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጎርፍ አደጋ በርካታ ጉዳት ለደረሰባት ሱዳን የተለያዩ ድጋፎችን በመያዝ ዛሬ ወደ ካርቱም እንደሚያቀና አል ዐይን አማርኛ ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የድጋፍ ቁሳቁሶችን ይዞ ወደ ካርቱም የሚያመራው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዑክ በሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራ ነው፡፡
የልዑኩ አባላት ካርቱም አየር ማረፊያ ሲደርሱ የሱዳን ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው የሱዳን ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ሱዳን በክረምቱ ከፍተኛ ዝናብ እና በዓባይ ወንዝ ሙላት በደረሰባት የጎርፍ አደጋ ከ100 በላይ ሰዎች የሞቱባት ሲሆን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ መፈናቀሉ ይታወሳል፡፡
በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ዉስጥ የምትገኘው ሱዳን በዋጋ ብረት እና በገንዘቧ የመግዛት አቅም መውረድም ክፉኛ በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ ተፈጥሯዊው የጎርፍ አደጋ ደግሞ ለሀገሪቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል፡፡ ሀገሪቱ ከዚህ ችግሯ እንድትወጣ ከፍተኛ ሰብዓዊ ድጋፍ ያደረገችውን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትም ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ የፖለቲካም ይሁን የኢኮኖሚ መረጋጋት የተሳናት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር መንግሥት ባለስልጣናት ሀገሪቱን ከቀውስ ለማውጣት ከሚወስዷቸው የተለያዩ እርምጃዎች በተጨማሪ የሀገሪቱ ስም ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር እንዲነሳ አሜሪካን በመወትወት ላይ ናቸው፡፡