ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 የተገደሉ ከፍተኛ ዓመራሮች የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
ከሩዋንዳ ድልድይ እስከ አትላስ ያለው ጎዳና በጄነራል ሰዓረ መኮንን ስም ተሰየመ
ለተሰዉት የአማራ ክልል እና የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች የመታሰቢያ ሃውልት እንደሚቆም ተገልጿል
ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 የተገደሉ ከፍተኛ ዓመራሮች የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት በባህር ዳር የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣የክልሉ ም/ቤት አፊ ጉባኤ ወርቅ ሰሞ ማሞ ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
አማራ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው በርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት ግቢ ዝክረ ሰማዕታት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡
ለተሰዉት የክልሉ መሪዎች የመተሰቢየ ሃውልት ለማቆም መሠረትም ተቀምጧል፡፡
የጄነራል ሰዓረ መኮንን 1ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕታት መርሀ ግብርም በዛሬው እለት የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
የጄነራል ሰዓረ መኮንን 1ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕታት ፕሮግራም አምና ከመስዋዕትነቱ በፊት በዛው እለት ከአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጋር ችግኝ በተከሉበት ቦታ ነው ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው፡፡
በስነስርዓቱ ላይ ከሩዋንዳ ድልድይ እስከ አትላስ ያለው ጎዳና በጄነራል ሰዓረ መኮንን ስም መሰየሙ ተገልጿል፡፡
በቀጣይም በጀነራሉ ስም ሃውልት እንደሚቆምላቸው እና በስማቸውም ፓርክ እንደሚሰራ መገለጹን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዘግቧል፡፡
በሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም ለተሰዉ ከፍተኛ አመራሮች የ1ኛ ዓመት መታሰቢያ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል።
በመቐለ ከተማም የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መሥተዳድር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ ዝክር ከ32ኛው የትግራይ ሰማዕታት ቀን ጋር በአንድነት ታስቧል፡፡
ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ በተመሳሳይ ሰዓት በተፈጸመ ጥቃት ነበር የአማራ ክልል እና የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ሕይወታቸውን ያጡት፡፡
በባህር ዳር በተፈጸመው ግድያ የወቅቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ፣ የ ርእሰ መሥተዳድሩ አማካሪ እዘዝ ዋሴ እና የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምግባሩ ከበደ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ደግሞ በግል ጠባቂያቸው በተተኮሰ ጥይት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና የሰራዊቱ የሎጂስቲክስ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት እና በጡረታ ላይየነበሩት ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ ተገድለዋል፡፡