“ዶ/ር ደብረጽዮን ለውይይት ነገ ኑ ብትሉንም ለመምጣት ዝግጁ ነን ብለውናል” የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት
“ዶ/ር ደብረጽዮን ለውይይት ነገ ኑ ብትሉንም ለመምጣት ዝግጁ ነን ብለውናል” የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት
ከሰሞኑ 43 ሰዎችን በማካተት ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ያመራው የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች በመቀሌ በነበራቸው ቆይታ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው እንደጠቀሱት በትግራይ ክልል ጥሩ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ የመማክርቱ ሊቀ መንበር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በመቀሌ ከተማ ከትግራይ ክልል እና ከፓርቲው አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡
በተደረገው ውይይትም በዋናነት የተበዳይነት ሥሜት መኖሩን መረዳታቸውንያነሱት ፕሮፌሰር መስፍን “ወደ መቀሌ ያመራነው ልዩነት ቢኖራችሁም እንደ አመራር ተገናኙና ተነጋገሩ ለማለት ነው” ብለዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት “ሁላችሁም አብራችሁ ያጠፋችሁ፣ አብራችሁ ያለማችሁ ናቸው በመሆኑም በጠረንጴዛ ዙሪያ ተወያዩ ፤ ችግሩንም ፍቱ” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን አንስተዋል፡፡
የትግራይ ክልል አራት አመራሮች ገለጻ ማድረጋቸውንና ጥር ሶስት ቀን ለፌዴራል መንግስት እንነጋገር የሚል ደብዳቤ መጻፋቸውን ለሀገር ሽማግሌዎች መማክርት መግለጻቸውን ነው ሰብሳቢው ያስታወቁት፡፡
በመጨረሻም የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሕወሓት ሊቀ መንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ”የሀገር ሽማግሌ እናከብራለን ለውይይት ነገ ኑ ብትሉንም መጥተን ለመወያየት ዝግጁ ነን” ማለታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ለሁሉም አካላት “የማትነጋገሩ ከሆነ ለህዝብ እንናገራለን” ማለታቸውን የገለጹት ፕ/ር መስፍን በመቀሌ ጥሩ አቀባበል እንደተደረገላቸውና የትግራይ ክልል መሪዎችም የሚሰማቸውን ሃሳብ መሰንዘራቸውን አስታውቀዋል፡፡
በትግራይ ክልል በኩል ከፌዴራል መንግስት ጋር ለመወያየት ዝግጁነት መኖሩን የገለጹት የሀገር ሽማግሌዎች ከመቀሌ እንደተመለሱም በአዲስ አበባ ከብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በዉይይቱም የብልጽግና አመራችም ከህወሓት ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን እንደገለጹላቸው ተናግረዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በሁለቱም ወገኖች መሰረታዊ ችግር እንደሌለና ዋነኛ ችግሩ ተቀራርቦ አለመነጋር መሆኑን ገልጿል፡፡
ሌላኛው ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ በሀገሪቱ ውይይት ሊዳብር እንደሚገባና ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ በነበረው የትግራይ ክልል ጉዞም ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም ወገኖች ፣ ማለትም ህወሃትም ብልጽግናም ፣ በጠረንጴዛ ዙሪያ ለመወያየትና ለመነጋር ዝግጁ መሆናቸውን ለሀገር ሽማግሌዎቹና ለሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል ነው የተባለው፡፡
ወደ መቀሌ ባመራው ልዑክ ውስጥ የሃይማኖት አባቶቹንና የሃገር ሽማግሌዎቹን ጨምሮ 43 አባገዳዎች፣ ኡጋሶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ተካተዋል፡፡ ሽማግሌዎቹ “ወደ መቀሌ ያመሩት በመንግስት ወይም በብልጽግና ፓርቲ አነሳሽነት ነው” መባሉ እንዳሳዘናቸው በጉባዔው በኩል መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡