የጌጣጌጡ መደበኛ የቀረጥና ታክስ ግምት ከ5 መቶ 60 ሺ ብር በላይ ነው
ቀረጥ ሳይከፈልበት ወደ ሃገር ሊገባ የነበረ የብር ጌጣጌጥ ተያዘ
ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት በቦሌ አለምአቀፍ አየርማረፊያ በኩል ወደ ሃገር ሊገባ የነበረ 15 ነጥብ 1 ኪሎ ግራም የብር ጌጣጌጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከዱባይ በሚመጡ መንገደኞች የተያዘ ነበር የተባለውን ጌጣጌጥ የአየር ማረፊያው ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰራተኞች ባደረጉት የአካል እና የኤክስሬይ ፍተሻ ጥር 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም ከተጠሪጣሪዎች ጋር መያዙ ተነግሯል፡፡
16 ሺ 724 የአሜሪካ ዶላር ዋጋ አለው የተባለለት ጌጣጌጡ የመደበኛ ቀረጥና ታክስ ግምቱ 566 ሺ 816 ብር ከ22 ሳንቲም ነው፡፡
በቁጥጥር ስር የዋለው 12 ኪሎ ግራም የብር ጌጣጌጥ በጃኬት መልክ በተሰራ ልብስ፣ 1 ነጥብ 1 ኪሎ ግራም በልብስ በመደብቅና፣ ቀሪው ሁለት ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ብር ደግሞ በድብቅ ለማስገባት ሲሞከር ነው የተያዘው፡፡
ጌጣጌጡን በማዘዋወር የተጠረጠሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን እና አንድ የውጭ ዜጋ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡