የደቡብ ክልል 5 ምዕራባዊ ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል ለመደራጀት ተስማሙ
ነባሩ ክልል ሲዳማን ጨምሮ በ5 አደረጃጀቶች እንዲዋቀር ምክረ ሃሳብ መቅረቡ የሚታወስ ነው
የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳው ምክር ቤቶች ከዚህ ቀደም የቀረበውን የአደረጃጀት ምክረ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል
የደቡብ ክልል 5 ምዕራባዊ ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል ለመደራጀት ተስማሙ
የምዕራብ ኦሞ፣ የሸካ፣ የከፋ፣ የዳውሮ፣የቤንች ሸኮ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳ በደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልልነት እንዲደራጁ የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ተቀበሉ፡፡
የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳው ምክር ቤቶች ዛሬ ባካሄዱት መደበኛ ጉባዔ በደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልልነት እንዲደራጁ ከአሁን ቀደም በመንግስት የቀረበውን ምክረ ሃሳብ በየምክር ቤቶቻቸው በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል፡፡
ከአሁን ቀደም በነበረው ክልላዊ አደረጃጀት የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ነበሩ ያሉት ምክር ቤቶቹ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ስነ ልቦና ቅርበት ያላቸው አካባቢዎች አንድ ላይ መደራጀታቸው የህዝብ አንድነትን የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ውሳኔው በቀጣይ ለክልሉ ምክር ቤት የሚቀርብ ሲሆን በቶሎ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍም ተወስኗል፡፡
ነባሩን የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በማፍረስ ከሲዳማ ክልል ውጭ በሶስት ክልሎች እና በአንድ ልዩ ዞን ለማደራጀት ከአሁን ቀደም የቀረበው ምክረ ሃሳብ ምዕራብ፣ ማዕከላዊ፣ ኦሞቲክ እና ጌዲኦ “ልዩ ዞን” የሚል ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ/ም ከነባሩ ክልል የየደረጃው አመራሮች ጋር ከተወያዩ በኋላ ምክረ ሃሳቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ምክር ቤቱም የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ይዞ እንዲቀርብ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑም አይዘነጋም።