አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጦርነቱ ለተጎዱ ትምህርት ቤቶች የ12 ሚሊዮን ድጋፍ ይዞ ነገ ወደ መቀሌ ያቀናል
ዩኒቨርስቲው ከኮሌጆቹ የሰበሰባቸውን የትምህርት ቁሳቁሶች ለትግራይ ትምህርት ቢሮ እንደሚያስረክብ ተናገረ
ድጋፉ በውድመትና ጉዳት ደጃቸውን ዘግተው የከረሙ የትምህርት ተቋማት ዳግም ማስተማር እንዲጀምሩ ያግዛል ተብሏል
በሰሜኑ ጦርነት ጉዳትና ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለማቋቋም ትምህርት ሚንስቴር ለዩኒቨርስቲዎች ጥሪ አቅርቧል።
ይህን ጥሪ ተቀብዬ ድጋፍ እያደረኩ ነው ያለው አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ ለትግራይ ዩኒቨርስቲዎችና ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቁሳቁሶችን ነገ ቅዳሜ ሰኔ 10፤ 2015 ዓ.ም. መቀሌ ተጉዞ እንደሚያስረክብ ለአል ዐይን አስታውቋል።
የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች አገልግሎትና አስተዳደር ም/ፕሬዝዳንት ማቲዎስ እንሰርሙ (ዶ/ር) ከኮሌጆች የተሰባሰበ አራት ተሽከርካሪ የመማሪያ ቁሳቁስ መቀሌ ይላካል ብለዋል።
አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ያወጣል የተባለው ድጋፍ፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ ፍራሽ እንዲሁም የላብራቶሪ ቁሳቁሶችን ያካተት መሆኑን ለአል ዐይን ተናግረዋል። 90 በመቶ የሚሆነው ድጋፉ ለትምህርት ክፍል የሚሆኑ መማሪያ ቁሳቁሶች እንደሆኑም አክለው ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርስቲው በዩኒቨርስቲዎች ኮንሰርቲየሙ (ህብረት) በኩል አንድ ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ፣ ለወደሙ ትምህርት ቤቶች ከራሱ ገቢ አስር ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ 12 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል።
ድጋፉ በውድመትና ጉዳት ደጃቸውን ዘግተው የከረሙ የትምህርት ተቋማት ዳግም ማስተማር እንዲጀምሩ እንደሚያግዝ ም/ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
“የሆነ ነገር ሊያግዝ ይችላል። ተጽዕና ላይፈጥር ይችላል። ግን ለተቸገ ሰው፤ ለተቸገረ ተቋም ትልቅ ነው። ሁሉም ተቋም ከተባበረ መቋቋም [ይችላል]። በቅርብ ጊዜ ትምህርት ሊጀምሩ ነው። እኛም ተርፎን ሳይሆን መጀመር ስላለባቸው ካለን ለማካፈል ነው። አንድ ሀገር ሙሉ የሚሆነው ሁሉም ሲማር ነው” ብለዋል።
እርዳታውን የትግራይ ትምህርት ቢሮ ተረክቦ ለተጎዱ ትምህርት ቤቶች እንደሚያከፋፍል ማቲዎስ እንሰርሙ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ቀጣይነት አለው የተባለው ድጋፉ በተለይም ለትግራይ ዩኒቨርስቲዎች በሰው ኃይል እገዛ እንደሚደረግ የጠቀሱት ም/ፕሬዝዳንቱ የምርምር፣ የመማር ማስተማርማ የፈተና እገዛ እንደሚደረግ ገልጸዋል።