ኢዜማና አብሮነት በምርጫው ጉዳይ ተቃራኒ አቋም ያዙ
ኢዜማና አብሮነት በምርጫው ጉዳይ ተቃራኒ አቋም ያዙ
ምርጫው መደረግ ይችላል -ኢዜማ
ምርጫ ተራዝሞ የሽግግር መንግስት ይቋቋም-አብሮነት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ምርጫ ይደረግ የሚል የመነሸ ሃሳብ ማቅረቡን ተከትሎ የሃገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ አቋም እያንጸባረቁ ይገኛሉ፡፡
ምርጫው ቢራዘምና የሽግግር መንግስት ቢመሰረት ለሃገር ደህንነት የተሸለ ነው የሚሉት በአንድ ወገን፣ የሃገሪቱን ሰላምና ጸጥታ በማረጋገጥ ምርጫውን ማድረግ ይቻላል የሚሉት ደግሞ በሌላ ወገን ሆነው ሃሳቦቻቸውን እያቀረቡ ነው፡፡
በዋናነት ሁለቱን ሃሳቦች እያቀረቡ ያሉት አብሮነትና ኢዜማ ሲሆኑ ለሃገሪቱ ይበጃል ያሉትን ሃሳብና ምክንያት አስቀምጠዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጊዜያዊነት ያስቀመጠውን የምርጫ ሰሌዳ በተመለከተ ሰፊ ግምገማ ማድረጉን የገለጸው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) ምርጫው እንዲራዘምና የእርቅና የሽግግር መንግስት እንድቋቋም ጠይቋል፡፡
ምርጫው እንዲራዘምና የሽግግር መንግስት ቢመሰረት ለሃገሪቱ ይበጃል ያለው አብሮነት፣ ይህ ካልሆነና በጥድፊያ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ ሃገሪቱ ወደ ከፋ ችግር ውስጥ ትገባለች ብሏል፡፡
ኢዜማ በበኩሉ መንግስት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መስራት አለበት፤ ከዛ በኋላ ግን ምርጫ ቢደረግ የተሻለ ነው የሚል ሃሳብ ያቀርባል፡፡
ኢዜማ ምርጫው ቢራዘምም የሃገሪቱ ችግር ሊፈታ አይችልም ስለዚህ ዋናው ጉዳይ መንግስት፣ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪዎቹም በሃገሪቱ ያለው የፖለቲካ ባህል እንድሻሻልና መረጋጋት እንድኖር ሊሰሩ ይገባል፣ ከዛም ምርጫው መደረግ አለበት ሲል አብሮነት ደግሞ ከዚህ የተቃረነ ነጥብ ይፋ አንስቷል፡፡
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ሃገሪቱ ከባድ ችግር ላይ ወድቃለች፡፡ በርካታ ፓርቲዎች ግን የኢትዮጵያ የወቅቱ ችግር አልገባቸውም ያለው ፓርቲው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ወደ ምርጫ መሄድ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ የማይቻል ነው ብሏል፡፡
አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት ተስኗቸዋል፣ የሃገሪቱ የትምህርት ተቋማት የጸጥታ ችግር አጋጥሟቸዋል የሚሉት ጉዳዮች በምክንያትነት ያነሳው አብሮነት እነዚህ ሁኔታዎች እያሉ ስለምርጫ ማሰብ አይቻልም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት ችግር ከዚህ ቀደም ካጋጠሟት ችግሮችና ውጣ ውረዶች አይበልጥም የሚል ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በመሆኑም ይህንን ችግር ለማለፍ መንግስ የሃገሪቱን ጸጥታ አስተማማኝ ማድረግ አለበት፣ አሁን ላይ እነዚህን ችግሮች ለማለፍ አስቸጋሪ አይደለም ብሏል ኢዜማ፡፡
የመንግስት አቅምና የሃገሪቱ ጸጥታ በፓርቲዎቹ ዕይታ
መጪው ሃገራዊ ምርጫ እንዲራዘምና የእርቅና የሽግግር መንግስት እንድቋቋም የጠየቀው አብሮነት ዋነኛ ምክንያት ያደረገው የሃገሪቱ ጸጥታ አስተማማኝ አለመሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ ኢዜማም አሁን ላይ ያለው የጸጥታ መደፍረስ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲል ያለውን ስጋት አስታውቋል፡፡
ሁለቱም ወገኖች በሃገሪቱ ችግር ላይ ስምምነት ቢኖራቸውም በቀላሉ ይፈታል አይፈታም በሚለው ጉዳይ ላይ ግን ተቃራኒ ሃሳብ ነው ያላቸው፡፡
አብሮነት መንግስት አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት አቅም አጥሮታል ሲል ኢዜማ አሁን ያለው ችግር ከመንግስት አቅም በላይ አይደለም ብሏል፡፡
በ 2012 ዓ/ም ምርጫው ይደረግ አይደረግ በሚል የአብሮነትንና ኢዜማን የሰሞኑን መግለጫዎች አካተትን እንጅ ሌሎች ፓርቲዎችም በዚሁ ጉዳይ ላይ ጋሳቦቻቸውን እየሰጡ ናቸው፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣የኦሮሞ ፌድራሊስ ኮንግረንስ (ኦፌኮ)ና ሌሎችም ምርጫው ይደረግ የሚል አቋም ይዘዋል፡፡
በሌላ በኩል ድግሞ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ በኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) እና በኅብር ኢትዮጵያ ደግሞ ሃገሪቱ ችግር ላይ በመሆኗ ምርጫ ሳይሆን የሽግግርና የዕርቅ መንግስት ይቋቋም የሚል ሃሳብ አንስተዋል፡፡