የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ፤ ወደሌላ የኃላፊነት መዛወራቸውን ገለጹ
በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የቢሮ ኃላፊው በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸው እየተገለጸ ነው
አቶ ዮናስ ሌላ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተገልጿል
የአዲስ አበባ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ በሌላ ኃላፊነት ላይ መሆናቸውን ገለጹ።
በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የቢሮ ኃላፊው በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸው እየተገለጸ ነው። አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው አቶ ዮናስ ከቢሮ ከወጡ አንድ ወር እንደሆናቸው ገልጸዋል።
አሁን ላይ ከኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊነት ወደ ሌላ የኃላፊነት ቦታ ላይ መዛወራቸውን ተናግረዋል። ይሁንና አሁን አለኝ ያሉትን ኃላፊነት አልገለጹም።
አቶ ዮናስ አሁን ላይ የኮሙኒኬሽን ቢሮው በአቶ አብዲ ጸጋዬ እየተመራ መሆኑንም ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል። አቶ ዮናስ ገዥው ብልፅግና ፓርቲን ወክለው ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የተወዳደሩ ሲሆን የም/ቤቱ አባልም ናቸው።
የወቅቱ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ ጸጋዬ ፤ አቶ ዮናስ ዘውዴ ከኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊነት መነሳታቸውንና ወደሌላ ቦታ መመደባቸውን ለአል ዐይን አረጋግጠዋል።
አቶ አብዲ፤ የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አሁን የተመደቡበት ቦታ መታወቁንና ደብዳቤውም ቢሯቸው እንደመጣ ገልጸዋል።
የወቅቱ የቢሮው ኃላፊ አሁን በስራ ምክንያት ከቢሮ ውጭ በመሆናቸው ወደ ቢሮ ሲመለሱ የአቶ ዮናስን አዲሱን ኃላፊነት እንደሚገልጹ ነው የተናገሩት።