“ኢትዮጵያውያን አሻንጉሊት መንግስት አይቀበሉም” - አዳነች አበቤ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ
በ“አሸባሪ”ነት የተፈረጀውን ህወሓት የሚያወግዝ እና የመከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተካሂዷል
“ጁንታው ወጣቶቻችንን በስናይፐር ገድሎብናልና ይህን ተግባሩን እንዲደግም አንፈቅድም”- ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” ብሎ የፈረጀውን ህወሓት የሚያወግዝ እና የመከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡
ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሰልፈኞች ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ ወደ መስቀል አደባባባይ የተመሙ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ፈረሰኞችም ተሳታፊ ሆነዋል ።
በሰልፉ የመከላከያ ሰራዊትን የሚደግፉ የተለያዩ መፈክሮችን ተሰምተዋል፡፡
በሰልፉ ላይ ከተያዙና ከተሰሙ መፈክሮች መካከል “ ለኢትዮጽያ አንድነት ዘብ እንቆማለን! በመስዋትነት የገነባናትን አገራችንን በመስዋዕትነት እንጠብቃታለን!፣ ጀግንነት እንጂ የባንዳነት ታሪክ የለንም!፣ ከዚህ በኋላ የሕወሐት ዝርፊያና የግድያ ተግባር የምንሸከምበት ትከሻ የለንም፣ ሸኔ የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ናት!፣ ለሕወሓት/ጁንታ መላላክ ከሃዲነትና ባንዳነት ነው!፣ ሕገ-መንግስቱንና ፌዴራላዊ ሥርዓቱን እንደ ዓይናችን ብሌን እንጠብቀዋለን!” የሚሉና ሌሎችም ይገኙበታል።
በሰልፉ ስነ-ስርአት የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ለሰልፈኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት “መስዕዋትነት በመክፈል ጭምር የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት በህዝቦቿ ትብብር እውን ይሆናል” ሲሉ ተደምጧል፡፡
“ጁንታው ወጣቶቻችንን በስናይፐር ገድሎብናልና ይህን ተግባሩን እንዲደግም አንፈቅድም” ያሉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ መስዕዋት እየከፈለ ላለው መከላከያ ሰራዊት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሽመልስ አክለው “ኢትዮጵያዊያን የትኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉ እና በራሳቸው ድምጽ ከመረጡት መንግስት ጋር ሆነው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ያስጠብቃሉ”ም ብሏል፡፡
“ኢትዮጵያውያን በድምፃቸው ማን ሊያስተዳድራቸው እንደሚገባ በመወሰናቸው ማንም የሚያስቀምጥላቸውን አሻንጉሊት መንግስት አይቀበሉም” ያሉት ደግሞ የአዲስ አባባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ናቸው፡፡
ምክትል ከንቲባዋ መከላከያ ሰራዊታችንና መላው የፀጥታ ሃይላችን የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ክብር ለመጠበቅ እየከፈሉ ያሉት ተጋድሎ እንዲጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለንም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት እያሰሙ ያሉት ድምጽ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ክብርና ነፃነት የሚሰማ የሚሊዮኖች ድምፅ በመሆኑ ሊከበር እንደሚገባ ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ በመስጠት ሰፊና ትዕግስት አስጨራሽ ትግል ሲያካሂድ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ፤ በመላው ህዝብ ትግል ከስልጣን የተወገደው የህወሓት ከሞተበት ለማንሳት የሚጥሩ የውጭ ጣልቃ ገቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ ጠይቀዋል።