በሰሜን ሽዋ በተቀሰቀሰ ግጭት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱን ነዋሪዎቸ ገለጹ
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች ዳግም ግጭት አገረሸ
ግጭቱ ከአንድ ሳምንት በፊት ተከስቶ በውይይት የተፈታ ቢሆንም ከትናንት ጀምሮ ዳግም ማገርሸቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች ዳግም ግጭት ማገርሸቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች ያሉ አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲከሰቱ ቆይተዋል፡፡
በአካባቢው በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ግጭቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ከአንድ ዓመት በኋላ ዳግም ግጭት ተከስቶ የሰው ህይወት ማለፉን ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ እንደተናገሩት ከአንድ ሳምንት በፊት በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ካሉ ወረዳዎች ውስጥ የቀወት ወረዳ አካል በሆነችው ኩሪብሪ ቀበሌ እና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ስራ ካሉ ወረዳዎች በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ወሰን ቁርቁር ቀበሌ አዋሳኝ ቦታዎች ግጭት ተከስቶ ነበር፡፡
በዚህ ግጭት የሰዎች ህይወት ባያልፍም ጉዳዩ ሳይስፋፋ በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ሀይል ተቆጣጥሮት እንደነበር ነዋሪው አክሏል፡፡
ከትናንት ማለትም ሚያዝያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከሰዓት በግምት 9 ሰዓት ጀምሮ ከሸዋ ሮቢት ከተማ ወደ ደሴ በሚያስኬደው ልዩ ስሙ የለን መገንጠያ እና ጀጀባ በሚል በሚጠሩ ስፍራዎች በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል ግጭት መፈጠሩን ነዋሪው ተናግረዋል፡፡
እንደ ነዋሪው ገለጻ ግጭቱ የተፈጠረው በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ስር ባለው ጅሌ ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች ተሸሽገው በቆዩ የሸኔ ታጣቂዎች እና በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ካሉት የቀወት ወረዳ እና ሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች መካከል ነው፡፡
የሸኔ ታጣቂዎች ከትናንት ጀምሮ ወደ ሸዋሮቢት ከተማ ለመግባት የጀመሩት ተኩስ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን ውጊያው በከባድ መሳሪያ የታገዘ መሆኑንም ነዋሪው ተናግረዋል፡፡
እንደ ነዋሪው ገለጻ እስከ አሁን ድረስ ከሁለቱም ወገን የስምንት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን የቆሰሉ ሰዎችም ወደ ህክምና ተቋማት መጥተዋል፡፡
ግጭቱን ለማስቆም የአካባቢዎቹ ፖሊስ እና ልዩ ሃይል ለማስቆም ሲጥሩ መመልከቱን የተናገረው ይህ አስተያየት ሰጪ መከላከያ እና ፌደራል ፖሊስ ግጭቶቹ ወዳሉባቸው አካባቢዎች እንዲገቡላቸው ጠይቋል፡፡
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ እና የሰንበቴ ከተማ ነዋሪ የሆነው ሌላኛው ነዋሪ ሰጪ በበኩሉ ከአዲስ አበባ እና ደብረብርሃን ወደ ደሴ የተደረጉ የትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች ከሸዋሮቢት ማለፍ ያልቻሉ ሲሆን ከደሴ ወደ አዲስ አበባ መስመር ይመጡ የነበሩት ደግሞ አጣዬ ላይ ቆመዋል ብሏል፡፡
ግጭቱን የጸጥታ ሀይል ገብቶ ያስቆመዋል በሚል ተስፋ የመንገዱን መከፈት ሲጠባበቁ የነበሩ አውቶብሶችም ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከአጣዬ ወደ ከሚሴ እና ደሴ በመመለስ ላይ መሆናቸውንም አስተያየት ሰጪው ነግሮናል፡፡
ስለግጭቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የአማራ ክልል ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ቢሮን ጨምሮ የሁለቱንም ዞኖች አስተዳድር ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡