በዓሉ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተከብሯል
127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በዛሬው እለት በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከብሮ ውሏል።
የዘንድሮው የድል በዓል “ዓድዋ የአንድነት፣ ጀግንነትና ፅናት ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው።
በዓሉን ምክንያት በማድረግም በአዲስ አበባ ንጋት ላይ መድፍ ተተኩሷል።
በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የተከበረ ሲሆን፤ በበዓሉ ላይም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ በተለያዩ ወታደራዊ ትርዒቶች አሳይተዋል።
በዓሉ በአዲስ አበባ ሚኒሊክ አደባባይ ማለዳ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዝውዴ እና አባት እና እናት አርበኞች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካዮች በተገኙበት የአበባ ጉንጉን የማኖር ስነ ስርዓት ተከናውኗል።
የአድዋ የድል በዓል በአዲስ አበባ አድዋ ድልድይም በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል።
ኢትዮጵያውያን በአጼ ሚኒሊክ እየተመሩ ቅኝ ሊገዛ የመጣውን የፋሽስት ወራሪ ኃይል በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ ድል አድርገው በመላው ጥቁር ህዝብ ድልነት የሚጠቀስ አዲስ ታሪክ መጻፋቸው የሚታወቅ ነው።