መሪዎቹ ሌሎች ሀገራትን ያካተተ የሰላም ቡድን የማቋቋም ፍላጎት አላቸው ተብሏል
በደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ የተመራ ልዑክ ዩክሬንን እና ሩሲያን ለማሸማገል በማለም ወደ ስፍራው አምርተዋል፡፡
በዚህ የሽምግልና መንገድ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ዛምቢያ፣ ኡጋንዳ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ሴኔጋል እና ኮሞሮስ መሪዎቹ የተውጣጡባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
አስቀድመው ወደ ዩክሬን ያመሩት እነዚህ የአፍሪካ መሪዎች ለዓለም ያስቸገረውን ጦርነት መቋጫ ይፈልጉለት ይሆን የሚለው ጉዳይ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡
እንግዶቹን መቀበል የጀመረችው ዩክሬን አስቀድማ ከሩሲያ ጋር ምንም አይነት የሰላም ስምምነት የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት በፕሬዝዳንቷ በኩላ ተናግራለች፡፡
መሪዎቹ የኪቭ ቆይታቸውን አጠናቀው ዛሬ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ለማግኘት ወደ ሞስኮ አቅንተዋል ተብሏል፡፡
ቢቢሲ የሰላም እና ፖለቲካ ተንታኞችን አነጋግሮ በሰራው ዘገባ የአፍሪካዊያን መሪዎች የጀመሩት የሰላም ጥረት ቻይናን፣ ቱርክን እና የካቶሊክ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
ደቡብ አፍሪካዊው የቀውስ ተንታኝ ኪንግስሊ ማኩብላ እንዳሉት አፍሪካ በሩሲያ እና ምዕራባዊያን ሀገራት ፍትጊያ እየተጎዳች ነው ብለዋል፡፡
መሪዎቹ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሚገባ አልተወከለችም ለሚለው አንድ ማሳይ ነው ያሉት ተንታኙ የአሁኑ ሙከራቸው ተሳክቶ ሰላም ማምጣት ከቻሉ ጥያቄው እውን እንዲሆን ጥሩ እድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል፡፡
የብራዛቪል ፋውንዴሽን ተንታኝ የሆኑት ጂያን ኦሊቨር በበኩላቸው ወደ ሞስኮ እና ኪቭ ያመሩት የአፍሪካ መሪዎች ምን አልባት ሁለቱ ሀገራት እስረኞችን እንዲለዋወጡ ሊያግዙ ይችሉ ካልሆነ በቀር ጦርነቱን ሊያስቆም የሚያስችል ድርድር ማድረግ አይችሉም ብለዋል፡፡
ከዚያ በተጨማሪ ከሩሲያ እና ዩክሬን የአፈር ማዳበሪያ እና ጥራጥሬ ምርቶች ወደ አፍሪካ እንዲጓጓዙ መፍትሄ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግኙነት የበለጠ በማሳደግ ከጥቂት ወራት በኋላ በምታካሂደው የሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤን በማስተናገድ ሞስኮ ከዓለም አለመነጠሏን ማሳየት ትፈልጋለች ተብሏል፡፡
አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ደግሞ አፍሪካዊያን ከሩሲያ ጎን እንዳይቆሙ የተለያዩ ጫናዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ ጎን ቆማለች በሚል በአሜሪካ የተወቀሰች ሲሆን የዋሸንግተን ህግ አውጪ አባላት ደቡብ አፍሪካ ለድርጊቷ መቀጣት አለባት እያሉ በመወትወት ላይ ይገኛሉ፡፡