የአፍሪካ ህብረት ከሳምንት በፊት አፍሪካውያንን እኩል አለማየት ተቀባይነት የለውም ማለቱ ይታወሳል
በዩክሬን ትምህርታቸውን የሚከታተሉ አፍሪካውያን ተማሪዎች በዩክሬን የተጀመረውን ጦርነት በመሸሽ ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመግባት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ እንግልት እና መገለል እየደረሳባቸው መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡
የናይጀሪያ የህክምና ተማሪ የሆነችው ኦዱኦላ አደቦዋሌ እንደተናገረችው እሷ እና ጓደኞቿ በባቡር ተሳፍረው ከዩክሬን ለመውጣት ሲሞክሩ ወታደሮች መሳሪያ ደቅነው እንዲመለሱ እንዳዘዟቸው መናገሯን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች በዩክሬን በትምህርት ላይ ነበሩ፡፡ ተማሪዎቹ የደረሰባቸውን መገለልና ጥቃት በተለያየ መንገድ እየገለጹ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረትም በአፍሪካውያን ተማሪዎች እየደረሰ ያለው ተግባር ትክክል አይደለም ብሏል፡፡
ህብረቱ ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ለደህንነታቸው በመፍራት ድንበር እንዳያቋርጡ በሚደረገው ተግባር ማዘኑን ገልጿል፡፡
በግጭት ጊዜ አለምአቀፍ ድንበር ማቋረጥ መብት መሆኑን የገለጸው ህብረቱ የቆዳ ቀለማቸው እና ዜግነታቸው ሳይታይ ለደህንነታቸው ድንበር የማቋረጥ መብት አላቸው ብሏል፡፡
ህብረቱ አፍሪካውያንን አንድ አይን አለማት ተቀባይነት የለውም፤ሁሉም ሀገራት አለምአቀፍ ህግን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ጠይቋል፡፡
የሩሲያ ጦር እስካሁን ባካሄደው “ዘመቻ” በደቡብ ዩክሬን የምትገኝው ኬርሶን ከተማ ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችንና ከተሞችን መቆጣጠር ችሏል፡፡ የሩሲያ ወታራዊ ዘመቻ በምዕራባውያን ዘንድ ያልተወደደ በመሆኑ በርካታ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ጎርፍ እየወረደባት ነው፡፡ ምዕራባውያን የኢኮኖሚ ማእቀብ ከመጣል በተጨማሪ የአየር ክልላቸውን ለሩሲያ ዝግ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው፣የኔቶ ጦር ዩክሬንን ጨምሮ ወደ ቀድሞ የሶቬት ህብረት ሀገራት እተሰፋፋ ነው፤ይህም ለደህንነቷ አስጊ እንደሚሆን በመግለጽ ነበር።የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እደቀጠለ ቢሆንም ሀገራቱ ችግሩን ለመፍታት ሁለተኛ ውይይታቸውን ጀምረዋል።
በምእራባውያን የምትደገፈው ዩክሬን፣ ምእራባውያን በዩክሬን ከበረራ ነጻ ቀጣና እንዲያውጁ ብትጠይቅም፤ ምእራባውያን ርምጃው ቢወሰድ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ ስለሚያጋጭ አናውጅም ብለዋል፡፡
ምእራባውያን ይህን ባለማድረጋቸው ዩክሬን ብቻዋን እየዋጋች ነው ሲሉ ዘለንስኪ ተደምጠዋል፡፡ ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ “በዩክሬን የተጀመረው ወታደራዊ ተልዕኮ” ሀገራቸው ባቀደችው መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡