ምዕራባውያን የኢኮኖሚ ማእቀብ ከመጣል በተጨማሪ የአየር ክልላቸውን ለሩሲያ ዝግ ማድረጋቸው ይታወሳል
የአውሮፓ ትልቁ የኒዩክለር ጣቢያ በሩሲያ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሉን የዩክሬን የክልል ባለስልጣናት አስታወቁ፡፡
የሩሲያ ጦር ዛፖሪዥያ በመባል የሚጠራውን ይህንን የኒዩክለር ማብላያ ጣቢያ መቆጣጠራቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው፡፡
- የሩሲያ ጦር በደቡብ ዩክሬን የምትገኝ ከተማ መቆጣጠሩን አስታወቀ
- ሁሉም አካላት ግጭቱን ከማባባስ ይታቀቡ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዩክሬኑ ቀውስ ላይ አስተያየት ሰጡ
ጣቢያው ከዓለም ትላልቅ ቆ የኒክለር ማብላያ ጣቢያዎች አንዱ ሲሆን ከአውሮፓ ደግሞ ትልቁ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህ የኒዩክለር ማብላያ ጣቢያ በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን ኢነርሆዳር ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡ ዛፖሪዥያ የሚባለው የኒዩክለር ጣቢያ በሩሲያ ኃይሎች ከመያዙ አስቀድሞ ቸርኖቭል የተባለውና በሰሜን ዩክሬን የሚገኘው የኒዩክለር ጣቢያም በሩሲያ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ዛፖሪዥያ 5700 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለሰንኪ ከፑቲን ጋር ፊት ለፊት መነጋገር እንደሚፈልጉ ከገለጹ በኋላ ነው ይህ የኒዩክለር ጣቢያ በሩሲያ እጅ የወደቀው፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ “በዩክሬን የተጀመረው ወታደራዊ ተልዕኮ” ሀገራቸው ባቀደችው መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ ጦር እስካሁን ባካሄደው “ዘመቻ” በደቡብ ዩክሬን የምትገኝው ኬርሶን ከተማ ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችንና ከተሞችን መቆጣጠር ችሏል፡፡ የሩሲያ ወታራዊ ዘመቻ በምዕራባውያን ዘንድ ያልተወደደ በመሆኑ በርካታ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ጎርፍ እየወረደባት ነው፡፡ ምዕራባውያን የኢኮኖሚ ማእቀብ ከመጣል በተጨማሪ የአየር ክልላቸውን ለሩሲያ ዝግ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው፣የኔቶ ጦር ዩክሬንን ጨምሮ ወደ ቀድሞ የሶቬት ህብረት ሀገራት እተሰፋፋ ነው፤ይህም ለደህንነቷ አስጊ እንደሚሆን በመግለጽ ነበር።
ከተጀመረ አንድ ሳምንት ባስቆጠረው ጦርነት፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዩክሬናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እደቀጠለ ቢሆንም ሀገራቱ ችግሩን ለመፍታት ሁለተኛ ውይይታቸውን ጀምረዋል።