ሞስኮ ዛሬ ከፊል ተኩስ አቁም አውጃለች
ምዕራባውያን አሁን ላይ እየጣሉት ካለው ማዕቀብ አንጻር “እንደ ሽፍታ እየሆኑ ነው” ስትል ሩሲያ ክስ አቀረበች።
ክሬምሊን ባወጣው መግለጫ ሩሲያን ከዓለም ለመነጠል በርካታ ማዕቀቦች ቢጣሉም ሩሲያ ግን ለመገለል በጣም ሩቅ ናት ብሏል።
ዓለም ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ እንደሚሰፋ ያነሳው የሩሲያ መንግስት አውሮፓውይን ስራቸው “እንደ ሽፍታ ሆኗል” ብሏል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፒስኮቭ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ለጣሉት ማዕቀብ መለስ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ቃል አቀባዩ ሀገራቸው ለተጣለባት ማዕቀብ ምላሽ እንደምትሰጥ ይግለጹ እንጅ ምን አይነት ማዕቀብ እንደሆነ ግን አልገለጹም ተብሏል። ይሁን እንጅ ሞስኮ ለተጣለባት ማዕቀብ የሀገሯን ብሔራዊ ጥቅም ግንዛቤ ውስጥ ያደረገ ተመጣጣኝ እርምጃ እርምጃ ትወስዳለች ነው ያሉት።
ምዕራባውያን ማዕቀብ ጣሉ ማለት ሩሲያ ከቀሪው ዓለም ተገለለች ማለት እንዳልሆነም ነው ዲሚትሪ ፒስኮቭ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
“አንድን ሀገር ለማግለል ዓለም ሰፊ ናት አትመችም” ያሉት ቃል አቀባዩ ከአሜሪካ እና አውሮፓ ውጭ ብዙ ሀገራት አሉ ሲሉም ገልጸዋል። ፒስኮቭ ይህንን ያሉት በጦርነቱ ምክንያት ሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን መነሻ በማድረግ ነው ተብሏል።
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገሮች፣ የኔቶ አባል ሀገሮች በሩሲያ ላይ ማዕቀብ እየጣሉ ሲሆን፤ ሞስኮ ግን በማዕቀብ “ጋጋታ” እንደማትዳከም እየገለጹ ናቸው።
ከተጀመረ 10 ቀን የሞላው ጦርነት ዓለምን እያነጋገረ ሲሆን ሩሲያ ማሪፖል እና ቮልኖቫካ በተባሉ ሁለት የዩክሬን ከተሞች ላይ ከፊል የተኩስ አቁም ማወጇ ተሰምቷል።
ሩሲያ በሁለቱም የዩክሬን ከተሞች ላይ ከፊል የተኩስ አቁም ያወጀችው የሰብአዊ እርዳታ ለማንቀስቀስ የሚያስችሉ ኮሪደሮችን ክፍት ለማድረግ በሚል እንደሆነ የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።