የአፍሪካ ህብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለተሳተፉ ተዋጊዎች አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ
በኢትዮጵያ ከ371 ሺህ በላይ ተዋጊዎች እንዳሉ ተገልጿል
የአውሮፓ ህብረት 12 ሚሊዮን ዩሮ ተዋጊዎችን ለመደገፍ ለኢትዮጵያ እሰጣለሁ ማለቱ ተገልጿል
የአፍሪካ ህብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ለመመለስ አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም ምክንያት የሆነው የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አንዱ አካል የሆነው የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲገቡ ማድረግ ዋነኛው ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ይህን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ለመተግበር ይረዳል ያለውን የአንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለኢትዮጵያ አድርጓል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ የሚባል ተቋም ያቋቋመ ሲሆን የመጀመሪያውን የበጀት ድጋፍ ለኢትዮጵያ አድርጓል፡፡
የድጋፍ ስምምነቱ ዛሬ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን ስምምነቱን የህብረቱ የፖለቲካ እና ሰላም ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ እና የኢትዪጵያ ብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር አምባሳደር ተሸመ ቶጋ ተፈራርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን የሰላም ስምምነት ለመተግበር በሚል ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አንዱ ሲሆን ኮሚሽኑ በመላው ሀገሪቱ ከ371 ሺህ በላይ ተዋጊዎች እንዳሉ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት ተዋጊዎች በራሳቸው ፈቃድ ትጥቅ ሲያወርዱ እና በሌሎች ምክንያቶች የቀድሞ ተዋጊዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ለመመለስ ሀብት በማሰባሰብ ላይ ነን ያሉት ኮሚሽነር ተሸመ ቶጋ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘነው የአንድ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ሌሎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ያነሳሳልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ብድር መክፈል ከማይችሉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ተካተተች
የአውሮፓ ህብረት የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት 16 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥ ቃል መግባቱን ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡
ትግራይ 55 ሺህ ተዋጊዎችን ማሰናበቱን የገለጹት አምባሳደር ተሸመ በኦሮሚያም በውጊያ ውስጥ የነበሩ ሰዎችን እያሰለጠኑ ወደ ህብረተሰቡ በመቀላቀል ላይ ናቸው በቀጣይ ግን ኮሚሽኑ በተደራጀ መንገድ ታጣቂዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው የመመለስ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
አምባሳደር ተሸመ አክለውም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ተዋጊዎችን ማሰልጠን እና ከህብረተሰቡ ጋር በማዋሃድ ወደ ቀድሞ ህይወታቸው መመለስ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለሁለት ዓመት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ እና አፋር ክልሎች ጦርነት የቆመ ቢሆንም በአማራ ክልል አዲስ ጦርነት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም ማደራጀት በሚል በወሰደው እርምጃ ምክንያት የተቀሰቀሰው ይህ ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ይገኛል፡፡