ሳንካራ እንዲገደል አሲረዋል በሚል የተጠረጠሩ 14 ሰዎች ችሎት መቅረብ ጀምረዋል
ቡርኪና ፋሶ ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ የቀድሞ ፕሬዝዳንቷን ገዳዮች ወደ ፍርድ አደባባይ ልታመጣ ሂደት መጀመሯን አስታወቀች።
ሀገሪቱ የቀድሞ መሪዋን ቶማስ ሳንካራን ገዳዮች ለፍርድ ማቅረብ መጀመራንም ሮይተርስ ዘግቧል።
የሚወዳትን ሀገሩን እየመራ የነበረው ቶማስ ሳንካራ አሰቃቂ በተባለ ግድያ ህይወቱ ቢያልፍም በበርካታ አፍሪካውያንና የአፍሪካ ወዳጆች ስሙ ጎልቶ ይነሳል።
በአራት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ተዓምር የሚያስብሉ ስራዎችን መስራቱንም በርካቶች ይመሰክራሉ። በአውሮፓውያኑ 1987 በቅርብ ወዳጁ ብሌስ ካምፓውሬ አስተባበሪነት በተመራ መፈንቅለ መንግስት የሳካራ ሕይወትና ስልጣን ተጠናቆ ነበር።
አፍሪካዊው ቼ ጉቬራ እየተባለ የሚጠራው ሳንካራ እንዲገደል አሲረዋል በሚል የተጠረጠሩ 14 ሰዎች ችሎት መቅረብ ጀምረዋል።
የቶማስ ሳንካራ ባለቤት ከ 34 ዓመታት በኋላ የሳንካራ ገዳዮች የፍርድ ሂደት መጀመር ስትጠብቀው የነበረ ሁኔታ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግራለች።
ችሎቱ በሚሰማበት ቦታ እንደደረሰች ለጋዜጠኞች በሰጠችው አስተያየት ይህ የፍርድ ሂደት መጀመር መፈንቅለ መንግስት በተደረገበትና ቶማስ ሳንካራ በተገደለበት አጋጣሚ ለተገደሉ 12 ሰዎችም ፍንጭ የሚሰጥ እንደሚሆን ተናግራለች።
የቀድሞው የቡርኪናፋሶ ፕሬዝዳንት የደህንነት ኃላፊ ካፋንዶ አንዱ የግድያ ተጠርጣሪ መሆኑ ቀደም ብሎ መነገሩ ይታወሳል።
የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትና የቶማስ ሳንካራ የቅርብ ወዳጅ ብሌስ ካምፓውሬ ዋነኛ የግድያው ተጠርጣሪ መሆናቸው ቀደም ብሎ የተዘገበ ቢሆንም ግለሰቡ ግን በዚህ ግድያ ላይ እጃቸው እንደሌለበት ተናግረዋል። ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ 100 ጋዜጠኞች የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል በሀገሪቱ ዋና ከተማ ኡጋዱጉ መገኘታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቶማስ ሳንካራ ባለ ራዕይ እና እውነተኛ አፍሪካዊ መሪ በሚል የሚወደስ ሲሆን፤ በፕሬዝዳንትነት ዘመኑ በብስክሌት በመሄድ የመንግስትንና የሀገርን ወጭ በመቀነሱ ስሙ ይነሳል። ለመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተብለው የተዘጋጁ መርሴድስ መኪኖችን በርካሽ ተሸከርካሪዎች በመቀየርም የሀገርን ወጭ እንደቀነሱ ይጠቀሳል።
ቶማስ ሳንካራ፤ ቡርኪናፋሶ ከቀድሞዋ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ጋር ያላት ግንኑነት እንዲበላሽ አድርጓል በሚል በኮምፓወሬ ይተቻል።በርካቶች ግን የቶማስ ሳንካራን መንገድ እንደሚደግፉ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
የሳንካራ የቅርብ ሰው የነበረው፤ በግድያው እንዳለበት የሚጠረጠረውና በኋላም ሀገሪቱን የመራው ኮምፓወሬ አሁን ላይ በኮትዲቯት እንደሚገኝ ተገልጿል።
የኮምፓወሬ የሕግ ሰዎች በኡጋዱጉ ፍርድ ቤት እንደማይታደም የገለጹ ሲሆን ኮትዲቯርም የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኗ ተገልጿል።