ጠንካራ ክርክር ያደገው የአማራ ክልል ምክርቤት በመጨረሻም ሹመቶችን አጸደቀ
ጠንካራ ክርክር ያደረገው የአማራ ክልል ምክርቤት በመጨረሻም ሹመቶችን አጸደቀ
አስቸኳይ ጉባኤ ያካሄደው የአማራ ክልል ምክርቤት በአዳዲስ ሹመቶች ላይ ጠንካራ ክርክር አድርጓል፡፡
አሁን ላይ በአማራ ክልል እያገለገሉ ያሉት ዮሀንስ ቧያለውና መላኩ አለበል ለምን ወደ ፌዴራል ይሄዳሉ የሚለው ጉዳይ የምክርቤቱን አባላት ለክርክር ጋብዞ ነበር፡፡
የምክርቤቱ አባለት በክልሉ አዲስ ሳይሆን ልምድ ያላቸው ክልሉን በደንብ የሚያውቁት በክልሉ ሊቆዩ ይገባል የሚል ድምጽ ከበርካታ የምክር ቤቱ አባለት ተስተጋብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አባለቱ ነባር አመራሮች ወደ ፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊነት መዛወር ክልሉን ያሚያዳክም ምናልባትም “ሴራ” ሊሆን ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ነገርግን አዳዲስ እጩዎችን በምክርቤቱ ፊት ያቀረቡት የአማራ ክልል ርእስ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ሹመቶቹን ማጽደቅ ወይንም ያለማጽደቅ የምክርቤቱ ዉሳኔ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደ ፌዴራል እንዲሄዱ የተደረገው በራሳቸው ዉሳኔ ሳይሆን “በፓርቲ” ዉሳኔ መሆን ተናግረዋል፡፡
የኃላፊዎቹ [ዮሀንስ ቧያለውና መላኩ አለበል] ወደ ፌዴራል የስራ ኃላፊነት መዛወር የራሳቸው ፍላጎትም እንደሆነ ርእሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ምክርቤቱ ለአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት በእጩነት የቀረቡትን ደ/ር ፋንታ ማንደፍሮ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡ በ136 ድምጽ ድጋፍ፣ በ3 ተቃውሞና 44 ድምጸ ተአቅቦ ሹመቱ ጸድቋል፡፡
አቶ አብየ ካሳሁንና ኃይለእየሱስ ተስፋማሪያም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት ሆነው ተሾመዋል፡፡
ምክርቤቱ ከዚህ በተጨማሪም የኦዲት፣ የንግድና ኢንቨስትመንትና ሌሎች የተለያዩ የካቢኔ አባላትን ሹመት አጽድቋል፡፡