“ዛሬ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንደኛ ደረጃ ዜጋ ናቸው”- አቶ አገኘሁ ተሻገር
የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ክልሎች ያካተተው 16ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች በዓል በድሬዳዋ እየተከበረ ነው

አቶ አገኘሁ የሞግዚት አስተዳደር ተጭኖባቸው ነበር ያሏቸው ክልሎች አስተዳደራዊ ነጻነት እንዳልነበራቸውም ነው የተናገሩት
የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ክልሎች ያካተተው 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በድሬዳዋ እየተከበረ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር እና ሌሎችም የፌዴራልና የድሬዳዋ አስተዳደር ባለስልጣናት በአከባበር ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
በዓሉ “ወራሪው የትግራይ ኃይል በመከላከያ ሰራዊት እና በህዝባዊ ጥምር ኃይል እየተቀጠቀጠ” ባለበት ሰዓት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ አገኘሁ ተሻገር ሃገራዊ አንድነታችን እኩልነትን በማይፈልገው የህወሓት ኃይል አደጋ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ስርዓት ለኢትዮጵያ ተስማሚ የአስተዳደር ዘይቤ ቢሆንም ህወሓት በመራባቸው ዓመታት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ተጨፍልቆ የአንድ ቡድን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እቅድ ማስፈጸሚያ ሆኖ ከመስተዋልም በላይ የባይተዋርነትና የተበዝባዥነት ስሜት የፈጠረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
አቶ አገኘሁ የሞግዚት አስተዳደር ተጭኖባቸው ነበር ያሏቸው ክልሎች አስተዳደራዊ ነጻነት እንዳልነበራቸውም ነው የተናገሩት፡፡
“እህትና አጋር ድርጅቶች በሚል ከፋፋይ ብያኔ” በኢትዮጵያ ጉዳይ አንዱ ቤተኛ ብዙሃኑ ባይተዋር ሆነው መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
“ዛሬ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንደኛ ደረጃ ዜጋ ናቸው”ም ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡
ለዚህም ከለውጡ ወዲህ በክልልነት ለመዋቀር የበቁትን ሲዳማንና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በማሳያነት አንስተዋል አፈ ጉባዔው፡፡
“ለእርስ በርስስ ጦርነት የተዳረግንባቸው ያለፉት 13 ወራት የቆምንበትን ምሰሶ ለመናድ ተሞከሮ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ወራሪ ያላነሰ ድርጊት ተፈጽሞ ያየነበት ነው”ያሉት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ጦርነቱን ተከትሎ የተስተዋለው ርብርብ “ጽኑ መሰረት ላይ መሆናችንንና በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጥሩ ደጀን መኖሩን ያሳየ” ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
13ቱ ወራት “የጦርነት ዋና ሰለባ እውነት ናት” መባሉ የተረጋገጠበት መሆኑን በማስታወስም በቂ መረጃ ሳይኖረን ከመጻፍና ከመናገር እንቆጠብ ሲሉ አደራ ብለዋል፡፡
አካታችና እውነተኛ ውይይት ምቹ የመግባቢያ መንገድ ነው ያሉም ሲሆን “ሃገራችን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት የራሳችንን ምላሽ እንፈልግ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለዚህም የመንፈስና የተግባር ዝግጁነት እንዲሁም የወደመውን መልሶ በመገንባት የወገኖችን ህይወት ወደነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ርብርብ እንደሚያስፈልግም ነው ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ የገለጹት፡፡
በዓሉ “ወንድማማችነት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ነው በተለያዩ ዐውደ ጥናቶችና የፓናል ውይይቶች በመከበር ላይ ነው፡፡
aXA6IDM1LjE3NS4xOTEuNDYg ejasoft island