ፖለቲካ
“የሃገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም ብቻ የድርድሩ መቃኛ ይሁን”-አል ቡርሃን
ሱዳን አዲስ የድርድር መንገድ ያስፈልጋል በሚል ከሶስትዮሽ ድርድሩ መውጣቷን ማስታወቋ ይታወሳል
የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ለሱዳን የግድቡ ተደራዳሪ ቡድን ድጋፋቸውን ሰጥተዋል
አል ቡርሃን ለሱዳን የግድቡ ተደራዳሪ ቡድን ድጋፋቸውን ሰጡ
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለሚደራደረው የሱዳን ቡድን ድጋፋቸውን ሰጡ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከተደራዳሪ ቡድኑ መሪ እና ከሃገሪቱ የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ የድርድሩን ሂደት የተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
ከገለጻው በኋላ የወጣው የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ መግለጫ ቡርሃን በቡድኑ የተያዘውን አቋም ደግፈዋል ብሏል፡፡
“የሱዳን ብሄራዊ ጥቅም ብቻ የድርድሩ መቃኛ እንዲሆን”ሲሉ ስለ ማሳሰባቸውም ነው ያስታወቀው፡፡
ቡርሃን የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው ያሉትን የመንግስትን አቋም ለመደገፍ የሚያስችሉ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ንቅናቄዎች እንደሚያስፈልጉም በአጽንኦት ስለመናገራቸው በሱዳን ትሪቢዩን ተዘግቧል፡፡
ሱዳን “አዲስ የድርድር መንገድ ያስፈልጋል ይህ ካልሆነ አልሳተፍም” በሚል ከሶስትዮሽ ድርድሩ መውጣቷን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
ለዚህ ጥያቄዋ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠኝም በሚል የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መውቀሷም አይዘነጋም፡፡