ተከሳሾቹ ይህን የጠየቁት “ለማንኛውም ጥቃት ተጋላጭ እንደሆንን እናምናለን” በሚል እንደሆነ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል
እነ አቶ ጃዋር መሃመድ ቃሊቲ አካባቢ ጊዜያዊ ችሎት እንዲቋቋምላቸው ጠየቁ
በከፍተኛ ወንጀሎች ተከሰው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የተከሰሱበትን ጉዳይ እየተከታተሉ ያሉት አቶ ጃዋር መሃመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ታስረው በሚገኙበት ቃሊቲ አካባቢ ጊዜያዊ ችሎት እንዲቋቋምላቸው ፍርድ ቤቱን ጠየቁ፡፡
ተከሳሾቹ በችሎት ለመቅረብ አለመቻላቸውን ጠቅሰው ትናንት ለፍርድ ቤቱ በጻፉት ደብዳቤ “ከተከሰስንበት ጉዳይ አወዛጋቢነት፣በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ካለን ሚና እና ሲነዛብን ከነበረው ሰፊ የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ አንጻር ለማንኛውም ጥቃት ተጋላጭ እንደሆንን እናምናለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“ከምንገኝበት እስር ቤት እስከ ልደታ ፍርድ ቤት ያለው ርቀትና የተጨናነቀ መንገድ ተጋላጭነታችንን ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል”ም ነው ያሉት፡፡
“በጉዞ ላይ ሊደርስብን ይችላል” ያሉት “ትንሽ የጥቃት ሙከራ” አሁን ካለው ፖለቲካዊ ትኩሳት ጋር ተዳምሮ ሃገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ሊወስዳት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ነው በደብዳቤው ያሰፈሩት፡፡
በመሆኑም “ምንም እንኳን የተፋጠነ ፍርድ ለማግኘት የምንሻ ቢሆንም ለአጠቃላይ ደህንነት ስንል የራሳችንን ፍላጎት ገትተን ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ/ም ቀጠሮ ላይ በችሎት ለመገኘት የማንችል መሆናችንን በትህትና እንገጻለን” ብለዋል፡፡
ለወደፊት ቀጠሮዎችም ቢሆን “በምንገኝበት አካባቢጊዜያዊ ችሎት እንዲቋቋምልን” ሲሉም ነው በደብዳቤው የጠየቁት፡፡
አቶ ጃዋር በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩት ለነበረው ኦ.ኤም.ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ጉዳዩን የተመለከተ የስልክ ማብራሪያ የሰጡት እና ከተከሳሾቹ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ከድር ቡሎ በደብዳቤው እንደገለጹት ሁሉ ተከሳሾቹ ዛሬ በነበራቸው ቀጠሮ ከችሎቱ ፊት አለመቅረባቸውን አረጋግጠዋል፡፡
“በተከሻሾቹ የተጻፈውን ደብዳቤ ለችሎቱ አቅርበናል”ያሉት አቶ ከድር ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለታህሳስ 8 ቀን 2013 ዓ/ም ቀጠሮ መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አባል እና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሃመድ እና አቶ በቀለ ገርባ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተቀሰቀሰው አመጽ እና ከሌሎችም ቀደም ሲል ተፈጽመዋል ከተባሉ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በፌዴራል ዐቃቤ ህግ ተከሰው ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡