ሰራዊቱ በያዛቸው የክልሉ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፎች መሰራጨት መጀመራቸውን መንግስት አስታውቋል
በትግራይ አራት የተፈናቃይ ጣቢያዎች ሊቋቋሙ ነው
በትግራይ ክልል አራት የተፈናቃይ ጣቢያዎችን በማቋቋም ላይ መሆኑን መንግስት አስታወቀ፡፡
ጣቢያዎቹ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ወደ ቀያቸው እስከሚመለሱ ድረስ የሚቆዩባቸው ናቸው ተብሏል፡፡
ጣቢያዎቹን የማቋቋሙን ሂደት የቴክኒክ ኮሚቴ እየተከታተለ ነው ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የሃገር መከላከያ ሰራዊት በቁጥጥር ስር ባዋላቸው የክልሉ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፎች መሰራጨት መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው መንግስት የተፈናቀሉትን ዜጎች በአፋጣኝ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ያለ ሲሆን በቴክኒክ ኮሚቴው ግምገማ መነሻነት ሰብዓዊ ድጋፎቹን በሰላም ሚኒስቴር እና በሌሎች የፌዴራል ተቋማት ትብብር ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ድጋፎች ጦሩ በያዛቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች መሰራጨት መጀመራቸውንም ነው ጽህፈት ቤቱ ያስታወቀው፡፡
በኮሚቴው ግምገማ መሰረት የእለት ደራሽ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉ የታመነበትም ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ድጋፎች ሁኔታዎች ወደ ቀደመ የተረጋጋ ይዞታቸው እስከሚመለሱ ድረስ መደረጋቸው ይቀጥል ተብሏል፡፡
ድጋፉ በሰላም ሚኒስቴር በኩል በሚዘጋጁ መንገዶች ይበልጥ ተደራጅተው እንደሚቀጥሉም ነው ወደ ቀያቸው የሚመለሱ ዜጎችን ለመደገፍ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት ጋር በትብብር እሰራለሁ ያለው መንግስት ያስታወቀው፡፡