አልሻባብ 170 የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ገደልኩ አለ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የአል-ሸባብን የሽብር ጥቃትን አውግዟል
ጅሃዳዊው ቡዱን በቪላ ሶማሊያ የከተመውን ማእከላዊ መንግስት ከስልጣን ለመገርሰስ የተለያዩ ጥቃቶች ሲሰነዝር ቆይቷል
አልሻባብ 170 የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ወታደሮችን ገድያለሁ አለ፡፡
በሶማሊያ ምድር የሚንቀሳቀሰው እስላማዊው ቡዱን ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ የተገደሉት ወታደሮች በየአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር ሆነው በሶማሊያ ተሰማርተው የነበሩ ቡሩንዳውያን ናቸው፡፡
የተገደሉት ወታደሮች ብዛት በተመለከተ እስካሁን ግልጽ የሆነ መረጃ ባይሰጥም፣ አንድ ከፍተኛ የቡሩንዲ ወታደራዊ አዛዥ ግን በጥቃቱ 30 መገደላቸው፣ 22 መቁሰላቸው እንዲሁም በርካቶች ያሉበት ስፋራ አለመታወቁ ተናግሯል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት፤ ወታደራዊ ስምሪት የሚሰጥበት ማእከል መቆጣጠሩን አልሻባብ አስታውቋል፡፡
ወታደራዊ የስምሪት ማእከሉ፤ ከመዲናዋ ሞቃዲሾ በስተሰሜን ምስራቅ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)፤ ወታደሮች እንደ ዋና ወታደራዊ የማዘዣና ስምሪት ማእከል ሲጠቀሙበት የነበረ ነው ተብለዋል፡፡
በአልሻባብ እና የአፍሪካ ህብረት ወታደሮች መከካል በወታደራዊ ማእከሉ በነበረው የቶክስ ልውውጥ በከባድ ብረትና ሄሊኮፕተሮች የታጀበ እንደነበር የሶማሊያ ወታደራዊ አመራር ኮማንደር ሞሐመድ አሊን ጠቅሶ ኤኤፍፒ ዘግቧል።
"በሁለቱም ወገን ሰዎች ሞተዋል፤ ከፍተኛ ውጊያ ነበ፤ ቦምብ በጫነ መኪና ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ የተኩስ ልውውጥ ነበር"ም ብሏል ኮማንደሩ።አልሻባብ ወታደራዊ የማዘዣ ማእከሉን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ቢገልጽም፤ ስለእውነታው እስካሁን በገለልተኛ አካል ተጣርቶ የተባለ ነገር የለም ፡፡
የሶማሊያ መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፤ የአል-ሸባብን የሽብር ጥቃት አውግዘዋል፡፡የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ህይወታቸውን የሰጡትን የብሩንዲ ወታደሮች አመስግነው ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ስር በሶማሊያ የተሰማሩ ጸጥታ አስከባሪዎች በዚህ ጥቃት ሳቢያ ዓላማቸው አይዛነፍምም ብሏል።
ህብረቱ ለሶማሊያ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልበትም ጭምር አረጋግጧል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአትሚስ የሚያደርገውን ድጋፍ በማጠናከር በሶማሊያ ሰላም እንዲወርድ እንዲያግዝም ሊቀ መንበሩ ጠይቋል። ጅሃዳዊው ቡዱን በቪላ ሶማሊያ የከተመውን ማእከላዊ መንግስት ከስልጣን ለመገርሰስ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ጥቃቶች ሲሰነዝር መቆየቱ ይታወሳል፡፡