ሶማሊያ ከአሜሪካ ኩባንያ ጋር የተደረገውን የነዳጅ ምርት ስምምነት ሰረዘች
የሃገሪቱ የፔትሮሊዬም ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ‘ኮስትላይን’ ከተባለ የአሜሪካ ነዳጅ አውጪ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመስራት መፈራረሙን አስታውቆ ነበር
ስምምነቱ በፕሬዝዳንት ፋርማጆ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ሮብል ነው የተሰረዘው
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ነዳጅ ፈልጎ እንዲያመርት ‘ኮስትላይን’ ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ሰረዙ፡፡
መሃመድ አብዱላሂ መሃመድ (ፋርማጆ) እና መሃመድ ሁሴን ሮብል እምብዛም ጊዜ ሳይፈጁ ነው ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በኩባንያው እና በሃገሪቱ የፔትሮሊዬም ሚኒስቴር የተፈረመውን ስምምነት የሰረዙት፡፡
በዕለቱ የፔትሮሊዬም ሚኒስትሩ አብዲረሽድ መሃመድ አህመድ ምርቱን እኩል በመጋራት መርሃ ግብር በሰባት የተለያዩ የባህር ዳርቻዎች ነዳጅ ፈልጎ እንዲያመርት ከ‘ኮስትላይን’ ጋር መስማማታቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
ሆኖም ስምምነቱ ከህግ ውጭ የተደረገ ነው በሚል በሃገሪቱ መሪዎች ተሰርዟል፡፡
“በምርጫ ወቅት ከውጭ አካላት ጋር ምንም ዐይነት ስምምነቶች እንዳይደረጉ በፕሬዝዳንቱ ተፈርሞ የወጣውን አዋጅ ይጥሳል”ም ነው የተባለው፡፡
የፔትሮሊዬም ሚኒስቴሩ ግን ስምምነቱ የነዳጅ ነው መባሉን ባወጣው መግለጫ አስተባብሏል፡፡ በሃገሪቱ ባህር ዳርቻዎች የሃይድሮካርበን ማዕድናትን ለማፈላለግ እንጂ ነዳጅን በሚመለከት እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡
እንደ መግለጫው ከሆነ መቀመጫውን አሜሪካ ቴክሳስ አድርጎ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከሚንቀሳቀሰው ኩባንያ ጋር የተደረሰው ስምምነት በአካባቢው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅም ላይ የተደረጉ የቅርብ ጊዜ ጥናቶችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡
ጥናቶቹ ላይ የተመሰረተው ስምምነት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ሶማሊያ ከነዳጅ አምራች ሃገራት ተርታ ልትሰለፍ እንደምትችል ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡