የሽብር ቡድኑ ለመግደል ያቀደው ፕሬዘዳንት መሀመድ ፋርማጆን እና ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሮብለን ነው
አልሻባብ የሶማሊያን ፕሬዘዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ለመግደል እያሴረ መሆኑን የሀገሪቱ ደህንነት አስታወቀ፡፡
በሶማሊያ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት በሚል የሚንቀሳቀሰው አልሻባብ የሽብር ቡድን የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት የመግደል እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡
የሶማሊያ ደህንነት በትዊተር ገጹ ባወጣው የማስጠንቀቂያ መልዕክቱ “አልሻባብ ፕሬዘዳንት መሀመድ ፋርማጆን እና ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሮብለን የመግደል እቅድ አውጥቷል” ብሏል፡፡
መሀመድ ማሂር የተሰኘው የአልሻባብ የሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራር ፕሬዚዳንቱን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል የቤት ስራ ወስዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም የሀገሪቱ የደህንነት ተቋም አስታውቋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ለመግደል ያቀደው በሶማሊያ እስላማዊ መንግስት የመመስረት እቅድ ስላለው መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል፡፡
ሶማሊያ የእንደራሴዎች ምክር ቤት እና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ባሳለፍነው ዓመት እቅድ የነበራት ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አራዝማለች፡፡
ምርጫው በመራዘሙ ምክንያትም በሀገሪቱ ለተፈጠረው አለመረጋጋት ዋነኛው ምክንያት ሲሆን በፕሬዚዳንቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ግጭት እንዲፈጠርም አድርጓል፡፡
አሜሪካም የሶማሊያ መሪዎች ምርጫውን አራዝማችኋል በሚል በሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ እቀባን ጨምሮ ሌሎች ማዕቀቦችን ጥላለች፡፡
አልሻባብ የተሰኘው የሽብር ቡድን በሶማሊያ እና ጎረቤት ሀገራት ዜጎች እና ተቋማት ላይ በርካታ ጉዳቶችን በማድረስ ላይ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት በሞቃዲሾ ባደረሰው የሽብር አደጋ የ48 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
በሶማሊያ ጠንካራ የመንግስት የደህንነት ተቋማት እንዲመሰረቱ በሚል በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ሰላም አስከባሪዎች በመቋዲሾ መሰማራታቸው ይታወሳል፡፡