ሩሲያ የጦር መሳሪያዎቿን በአልጀሪያ በኩል ለአፍሪካ ሀገራት እንደምትሸጥ ይገለጻል
ሩሲያ እና አልጀሪያ በሜድትራኒያን ባህር ላይ ወታደራዊ ልምምድ አካሄዱ።
ከምዕራባዊያን ጋር ግጭት ውስጥ ያለችው ሩሲያ ከአልጀሪያ ጋር የጦር ልምምድ ማድረጓ ተገልጿል።
የአልጀሪያ እና ሩሲያ የባህር ሀይሎች በሜድትራኒያን ባህር ላይ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውን የሁለቱም ሀገራት ብዙሀን መገናኛዎች ዘግበዋል።
ይህ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮውን የባህር ላይ ልምምድ ባሳለፍነው ማክሰኞ ጀምረው ትናንት አጠናቀዋል ተብሏል።
በምስራቃዊ ሜድትራኒያን ባህር ልዩ ስፍራው ጅጄል ወደብ አቅራቢያ የተካሄደው ይህ ልምምድ ዓላማው የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ማጠናከር ያለመ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም የባህር ላይ ውንብድና እና ሌሎች የባህር ላይ ወንጀሎችን መከላከል ላይ ማተኮሩ ተገልጿል።
ሩሲያ በአፍሪካ ካሉ ቁልፍ ወዳጅ ሀገራት መካከል አልጀሪያ አንዷ ስትሆን በተለይም የሩሲያን የጦር መሳሪያ ለሚፈልጉ የአፍሪካ ሀገራት አልጀርስ ዋነኛዋ መገበያያ ከተማ እንደሆነች ተጠቅሷል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገቡ ስምንት ወራት ሆኗቸዋል።
ጦርነቱን ተከትሎም የአውሮፓ ህብረትን እና አሜሪካንን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀብ ተጥሎባታል።
ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ወዳጅ አይደሉም ላለቻቸው ሀገራት በሩብል ነዳጅ እንዲገዙ ከማድረግ ጀምሮ ብዙ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች።