ቼልሲ ከቤነፊካ ኢንዞ ፈርናንዴዝን በ107 ሚሊየን ፓውንድ በማስፈረሙ የጥር ወር የሊጉ የዝውውር ክብረወሰን ተሰብሯል
በጥር ወር የዝውውር መስኮት አዲስ ክብረወሰን ተመዘገበ
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የጥር ወር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት አዲስ ክብረወሰን ተመዝግቦበታል።
ትናንት ምሽት በተጠናቀቀው የዝውውር ጊዜ ክለቦች 815 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ በማድረጋቸው ነው አዲስ ክብረወሰን የተያዘው።
ቼልሲ አርጀንቲናዊውን አማካይ ኢንዞ ፈርናንዴዝ ከቤነፊካ በ107 ሚሊየን ፓውንድ ማስፈረሙም የጥር ወር የሊጉ የዝውውር ክብረወሰን እንዲሰበር አድርጓል።
በትናንቱ የዝውውር መዝጊያ እለት ብቻ 275 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ የተደረገባቸው የተጫዋቾች ዝውውሮች ተደርገዋል።
ትናንት ብቻ የተመዘገበው ዝውውር በ2018 ተይዞ ከነበረው የጥር ወር ከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ (180 ሚሊየን ፓውንድ) የ83 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በአጠቃላይ በክረምቱ እና በጥር ወር የ2022 – 2023 የዝውውር ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ ክለቦች ያወጡት ወጪም 2 ነጥብ 8 ቢሊየን መድረሱን ነው ጎል ዶት ኮም ያስነበበው።
ቼልሲ በጥር ወር ዝውውር ያወጣው 323 ሚሊየን ፓውንድ ከሁሉም የጀርመን፣ ስፔን፣ ጣሊያን እና ፈረንሳይ ሊግ ክለቦች የጥር ወር የዝውውር ወጪ የሚልቅ ነው።
በዝውውሩ መዝጊያ እለት እነማን ፈረሙ?
ቼልሲ ከቤነፊካ ኢንዞ ፈርናንዴዝን በ107 ሚሊየን ፓውንድ ያስፈረመበት ዜና ትልቁ ነበር።
የሊጉ መሪ አርሰናልም በ12 ሚሊየን ፓውንድ ጣሊያናዊውን አማካይ ጆርጊንሆ ከሰማያዊዮቹ አስፈርሟል።
በሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ የማርሴል ሳቢትዘርን የውሰት ውል አጠናቆ ከባየ ሙኒክ ወደ ኦልትራፎርድ አዛውሯል።
ቶተንሃምም ፔድሮ ፖሮን ከስፖርቲንግ ሊዝበን በውሰት አስፈርሟል። የውድድር ጊዜው ሲጠናቀቀም 40 ሚሊየን ፓውንድ ከፍሎ በእጁ ሊያስገባው ነው የተፈራረመው።
የክለቡን ክብረወሰን በሰበረ 22 ሚሊየን ፓውንድ ጋናዊውን ካማልደን ሱሌማናን ዝውውር ያጠናቀቀው ሳውዛምፕተንም በጥር ወር የዝውውር ጊዜ የመጨረሻ እለት ርብርብ ካደረጉ ክለቦች መካከል ተጠቃሽ ነው።
በርንማውዝ፣ ሌስተር ሲቲ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት እና ክሪስታል ፓላስም ተጫዋቾችን በማስፈረም የሊጉ የጥር ወር የዝውውር ክብረወሰን እንዲሰበር ተሳትፎ አድርገዋል።
ለአሜሪካዊው ባለሃብት ቶድ ቦህሊ የተሸጠው ቼልሲ በጥር ወር ዝውውር ስምንት ተጫዋቾችን በማስፈረም ቀዳሚውን ደረጃ ይዟል።
ሰማያዊዮቹ ያወጡት የዝውውር ወጪም ከአጠቃላይ የሊጉ ክለቦች 37 በመቶውን ድርሻ ይይዛል።