ኢትዮጵያ ከ59 ዓመታት በፊት ያወጣችውን የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ህግ ልታሻሽል ነው
በቀረበለት ረቂቅ ላይ የመከረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል
ህጉ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ካለመጣጣም ባሻገር ሃገሪቱ የምትከተለውን የፌዴራል ስርዓት ያላገናዘበ ነው ተብሏል
ኢትዮጵያ ከ59 ዓመታት በፊት ያወጣችውን የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ህግ ልታሻሽል ነው
90ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት ያካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅ እንዲሻሻል ወስኗል፡፡
አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ህግ በ1954 ዓ/ም የወጣው ነው ያለው ምክር ቤቱ አሃዳዊ አወቃቀርና የአስተዳደር ስርዓትን የተከተለ በመሆኑ ሃገሪቱ የተገበረችውን የፌዴራል ስርዓትና በክልሎች እና በፌዴራል መንግስታት መካከል ያለውን ህገመንግስታዊ የስልጣን ክፍፍል ያላገናዘበ ነው ተብሏል፡፡
ሃገሪቱ በርካታ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች በተለይም የሲቪልና የፖለቲካ፣የህጻናት እና የሴቶች መብቶች እንዲሁም ሌሎች መብቶችን የተመለከቱ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ተቀብላ የሃገሪቱ ህግ አካል አድርጋቸዋለች ያለም ሲሆን እነዚህን ለውጦች ያገናዘበ እና በስራ ላይ ካሉት ህጎች ጋር የተጣጣመ ለውጥ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በስራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርዓት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ግልጽነት የጎደለው ነው እንደ ምክር ቤቱ ገለጻ፡፡
ዛሬ ላይ ከሚፈጸሙ ውስብስብና የረቀቁ ወንጀሎች አንጻር እንዲሁም ዘመኑ ከደረሰበት የወንጀል ሳይንስ ጋር አብረው የማይሄዱ በርካታ ድንጋጌዎች የተካተቱበትና መሰረታዊ ክፍተት ያለበትም ነው፡፡
እንደዚሁም ህብረተሰቡ የወንጀል ጉዳዮችን የሚፈታባቸው የዳበሩ ስርዓቶች ያሉት ቢሆንም በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጉ ውስጥ በአግባቡ አልተካተቱም፡፡
በዚህም ምክንያት በ1954 ዓ/ም የወጣውና በስራ ላይ የዋለው ህጉ በዘመናዊም ሆነ በባህላዊ አግባብ የሚታዩ እድገቶችንና ተግባሮችን አሟቶ ያልያዘ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል፡፡
በመሆኑም ከህገ መንግስቱ፣ ከፌዴራል ስርዓቱ፣ ከዓለም አቀፍ ህጎች እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ካላቸው የዘመኑ አሰራሮች ጋር የተጣጣመ አዋጅ ተዘጋጅቶ የወንጀል ስነ ስርዓት ህግ እና የማስረጃ ህግ ማውጣት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር የተወያየው ምክር ቤቱም ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
የአዋጁ መሻሻል በፌደራል ሥርዓት ውስጥ የሚና እና የኃላፊነት ክፍፍል በአግባቡ እንዲከናወን የሚረዳ ወሳኝ ርምጃ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ውሳኔውን አድንቀዋል።
ምክር ቤቱ የግልግል ዳኝነትን እና የዕርቅ አሠራር ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ ደንብን ጨምሮ በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ዐበይት ውሳኔዎችን ስለማሳለፉም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።