ጆሴፕ ቦረል በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አደራዳሪነት ያላቸው እምነትም ገልጸዋል
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተሳተፉ የሚገኙት ሁሉም ወገኖች ጦርነቱን ማቆም አለባቸው ሲሉ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ፣ ደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦረል ኣሳሰቡ፡፡
ጆሴፕ ቦረል አክለው “የጦርነቱ ተዋናዮች በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይዳረስ የጣሉት እገዳ ሊያነሱ እንዲሁም ከጥላቻ ንግግር ሊቆጠቡ ይገባል” ሲሉም በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አጋርቷል፡፡
ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚካሄደውን የተኩስ አቁም ድርድርን ለመምራት የተሻሉ ናቸውም ነው ያሉት አውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ፣ ደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦረል።
በሰሜን ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት “በቅርቡ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ተደርገው መሾማቸው” የሚታወስ ነው፡፡
ህብረቱ በከፍተኛ ተወካዩ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግስትን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እየመከረ መሆኑን በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶየ ከሳምንት በፊት ለአል-ዐይን ኒውስ ተናግረው ነበር፡፡
ኮሚሽነሩ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች መሰረት “ሁሉም የግጭቱ ተዋናዮች በመጨረሻ ወደ ጠረጴዛ እንደሚመጡ ትልቅ ተስፋ አለን” ማለታቸውም አይዘነጋም።
ጥቅምት ወር 2013 የህወሓት ሃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጀው “ህግ ማስከበር ዘመቻ” ተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ዓመት ሊሆነው ጥቂት ቀናት ቀርተውታል፡፡
አሁን ላይ ጦርነቱ ወደ ጎረቤት ክልሎች በመስፋቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ተፈናቅለው ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡
ጦርነቱ የፈጠረውን ቀውስ እንዲቆም፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስትን ጨምሮ የግጭቱ ተዋናዮች ተኩስ አቁምው ወደ ድርድር እንዲመጡ በተለያዩ ደረጃዎች ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑም የሚታወቅ ነው፡፡