የትግራይ ግጭትን የተመለከተው የተመድ እና የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት ጥቅምት 24 ይፋ ይሆናል ተባለ
በዕለቱ ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሚሼል ባሼሌት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሏል
ሪፖርቱ ይፋ በሚሆንበት ዕለት የሰሜን ዕዝ ጥቃት አንድ ዓመት ይሞላዋል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር በትግራይ ግጭት ላይ ሲያደርገው የነበረው ምርመራ ሪፖርት በመጪው ረቡዕ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ/ም (3 November 2021) ይፋ እንደሚሆን አስታወቀ፡፡
ሪፖርቱ ሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ/ም (1 November 2021) ይፋ እንደሚደረግ ነበር ከአሁን ቀደም ሲገለጽ የነበረው፡፡
አሁን ግን በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት ትግራይ ይገኝ በነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ዕለት ነው ይፋ የሚደረገው፡፡ጥቃቱ በመጪው ረቡዕ አንድ ዓመት ይሞላዋል፡፡
የማይካራው ጭፍጨፋ “ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን” መፈጸሙን ኢሰመኮ ገለጸ
ተቋማቱ ጥቃቱን ተከትሎ ተፈጽመዋል የተባሉ የግድያ፣ የአስገድዶ መድፈር እና ሌሎችንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በጋራ ሲመረምሩ ቆይተዋል፡፡
ከፈረንጆቹ ግንቦት 16 እስከ ነሀሴ 20 ቀን 2021 ድረስም ከ200 በላይ ሰዎችን ቃለመጠይቅ ማድረጋቸውን ገልጸውም ነበር፡፡
የምርመራው የመስክ ስራ የተካሄደው በመቀሌ፣ ውቅሮ፣ ሳምረ፣ አላማጣ፣ ቦራ፣ ማይጨው፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ፣ ሁመራ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር እና አዲስ አበባ ከተሞች ነው እንደ ኢሰመኮ ገለጻ፡፡
በምርመራው በግጭቱ የተጎዱ ሰዎች፣ የአይን ምሰክሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት እንዲሁም የክልል እና የፌደራል ተቋማት ሰራተኞች፤ አመራሮች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ የፍትህ አካላት እና ሌሎች ስለ ጉዳዩ ያውቃሉ የተባሉ አካላት ተጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም የምስል እና የሰነድ ማስረጃዎች፣ ቪዲዮዎችን እና ሌሎች ለምርመራ ይጠቅማሉ የተባሉ መረጃዎችን ሁሉ ተሰባስበዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የዘንድሮውን የጀርመን አፍሪካ ሽልማት አሸነፉ
ሪፖርቱ ይፋ በሚሆንበት ጊዜ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሚሼል ባሼሌት ከአዲስ አበባ እና ከስዊዘርላንድ ጄኔቭ ሆነው ጋዜጣዊ መግለጫን እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡
በመግለጫው የሪፖርቱ ግኝቶች እንደሚቀርቡ እና ማጠቃለያና ምክረ ሃሳብ እንደሚሰጥም ነው ኢሰመኮ ለአል ዐይን አማርኛ በላከው መግለጫ ያስታወቀው፡፡