“ምርጫው በአመዛኙ ሰላማዊ ቢሆንም ከችግሮች የራቀ አልነበረም”- የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
ሆኖም በተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ጥቃት ያደረሱ በአፋጣኝ እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርቧል
የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊና በብዙ መልኩ የተሳካ ነበር ያለው ኮሚሽኑ የጎሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አለመስተዋላቸውን አስታውቋል
በተደራረቡ ሃገራዊ ችግሮች አውድ ውስጥ ሆኖ የተካሄደው 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ያለ ጎላ ችግር መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኢሰመኮ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንደነበር አስታውቋል።
ኮሚሽኑ 94 ባለሙያዎችን የያዙ 35 የክትትል ቡድኖች በማሰማራት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ምርጫው በተካሄደባቸው 7 ክልሎች በሚገኙ 99 ምርጫ ክልሎች እና 404 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ክትትል አድርጌያለሁ ብሏል፡፡
በክትትሉ በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው እለት ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተቶችን ተመልክቷል፡፡
ሆኖም በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳልነበሩ ነው ኮሚሽኑ የምርጫውን ሂደት አስመልክቶ ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ያሰፈረው።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ “በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የምርጫው ዕለት ሂደት ያለ የጎላ ችግር በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀ በመሆኑ፤ የምርጫው ዕለት ሂደት ሰላማዊ፣ ሥርዓትን የተከተለና በአብዛኛው ሁኔታ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩበትና በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ነበር” ብሏል።
ሆኖም “አወንታዊና አበረታች ናቸው” ያላቸው እነዚህ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እንዲሁም በፀጥታ ኃይሎች እና በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነው የጠቆመው፡፡
“ጥቃቱን የፈጸሙ፣ ግድያና የአካል ጉዳት፣ እስርና እንግልት ያደረሱ ሰዎችላይ ሁሉ በአፋጣኝ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ”ም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ ምርጫ ቦርድ ለክትትል ባለሙያዎቹ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ለመግባት የሚያስችላቸውን ካርድ (ባጅ) ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት በየምርጫ ጣቢያዎቹ ያለውን ሁኔታ በወጉ ለመከታተል ተቸግሮ እንደነበርም ነው ያስታወቀው፡፡
የምርጫውን መካሄድና በሚሊዬኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በምርጫው መሳተፋቸውን ያወደሱት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) ክትትል ባደረግንባቸው ቦታዎች የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ባንመለከትም ጥሰቶች እንደነበሩ ግን ሃቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምርጫው ይበጃሉ ያላቸውን ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎች ቀድሞ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡