በአለማችን ከ55 ሚሊየን በላይ ሰዎች በዚሁ በሽታ ተጠቂ ናቸው
ለመጀመሪያ ጊዜ የአዕምሮን በመርሳት በሽታ ወይም አልዛይመር መጠቃት ለመቀነስ የሚያግዝ መድሃኒት ተገኝቷል።
ላካኔማብ የተሰኘው መድሃኒት ለረጅም ጊዜ ተሞክሮ አልሳካ ብሎ የቆየውን የመርሳት በሽታ አስቀድሞ ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሏል።
ኢሳይ እና ባዮጂን በተባለ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የተሰራው መድሃኒት በአልዛይመር በሽታ ህክምና ላይ ፈር ቀዳጅ ስለመሆኑ ነው ተመራማሪዎች የተናገሩት።
በብሪታንያ የአልዛይመር በሽታ ጥናት የሚያደርግ ተቋም ለአመታት ሲደረግ የቆየውን ውጤት አልባ ምርምር የቀየረ አስደናቂ ግኝት ነው ብሎታል።
ላካኔማብ የመርሳት በሽታ ተጠቂ በሆኑ ሰዎች አዕምሮ ላይ የሚታየውን ቤታ አምሎይድ የተሰኘ ፕሮቲን የሚቀንስ ነው።
መድሃኒቱ የመርሳት በሽታው ሳይጠነክር የሚሰጥ መሆኑና በርካቶች ሳያውቁት ለበሽታው ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ግን አሁንም ባለሙያዎቹን እያከራከረ ነው።
ከ30 አመት በላይ በዚሁ ህመም ላይ ምርምር ያደርጉት ፕሮፌሰር ጆን ሃርዲይ ግን መድሃኒቱ ታሪካዊ እና እጅግ ተሰፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
በኤዲንበርግ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁር ፕሮፌሰር ታራ ጆንስም ከዚህ በፊት የነበረውን መቶ በመቶ ያልተሳካ ሙከራ በላካኔምባ መድሃኒት ተለውጧል ነው ያሉት።
በ1 ሺህ 795 የመጀመሪያ ደረጃ የአልዛይመር ተጠቂዎች ላይ መዲሃኒቱ ተሞክሮ የተገኘው ውጤትም ተስፋ ሰጪ መሆኑን አብራርተዋል።
መድሃኒቱ ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ባይፈውስ እንኳን የጉዳት መጠኑን በእጅጉ መቀነሱንም ነው ፕሮፈስር ታራ ጆንስ ለቢቢሲ የተናገሩት።
በአሜሪካ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሙያዎች ፍተሻ እየተደረገበት ያለው የመርሳት በሽታ መድሃኒት ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ጥቅም ላይ እንዲውል ታቅዷል።
በበሽታው ክፉኛ የተጎዱ ሰዎችም የመድሃኒቱን ለገበያ መቅረብ እየተጠባበቁ ነው።
በአለማችን ከ55 ሚሊየን በላይ ሰዎች በአልዛይመር ተጠቂ መሆናቸው ይነገራል።
የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር በ2050ም ወደ 139 ሚሊየን እንደሚደርስ ነው የሚገመተው።
ለ18 ወራት ተሞክሮ አስደናቂ ውጤት አሳይቷል የተባለው የበሽታው መድሃኒት ጉዳይም የዘርፉን ባለሙያዎች በሁለት ጎራ ከፍሎ እያከራከረ ቢሆንም የሚሊዮኖች ተስፋ ሆኗል።