በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን አለፈ
በደሴ እና ኮምቦልቻ ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች በድጋሚ መፈናቀላቸው የሀብት እጥረቱን እንዳባበሰው ተገልጿል
ህወሃት በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አይታወቅም ተብሏል
በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን አለፈ፡፡
የአገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉን ተከትሎ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሃት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች አዲስ ጥቃት መክፈቱ ይታወሳል፡፡
በአማራ ክልል አራት ሚሊዬን ዜጎች ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ
በዚህ ጦርነት ምክንያትም በአማራ ክልል ብቻ 1 ነጥብ 14 ሚሊዮን ዜጎች ሲፈናቀሉ 918 ሺህ ዜጎች ደግሞ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ በአማራ ክልል የተፈናቀሉ እና ለእለት እርዳታ የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር 2 ሚሊዮን 55 ሺህ ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡
በተቋሙ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ጀምበሩ ደሴ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት በህወሃት ጥቃት ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡
ከዋግ እና ሰሜን ወሎ ወረዳዎች ተፈናቅለው በደሴ እና ኮምቦልቻ ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች በድጋሚ መፈናቀላቸው የሀብት እጥረቱን እንዳባበሰውም አቶ ጀምበሩ አክለዋል፡፡
መንግስት አጋር ድርጅቶች ለአማራና አፋር ክልሎች የሚያደርጉትን ድጋፍ መጠን ከፍ እንዲያደርጉ ጠየቀ
በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ከ500 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው ለ300 ሺህ ያህሉ ለአንድ ወር የሚበቃ ምግብ እና ሌሎች አልባሳት አድርሰን ነበር የሚሉት አቶ ጀምበሩ የህወሃት ተዋጊዎች ወደከተሞቹ መግባታቸውን ተከትሎ “የሰጠናቸውን ድጋፍ ትተው ወደ ደብረብርሃን እና ሌሎች ቦታዎች ተሰደዋል” ብለዋል፡፡
ይህ መሆኑ “በፊትም የነበረብንን የሀብት እጥረት የባሰ አክብዶብናል”ም አቶ ጀምበሩ ያሉት፡፡
አሁን ላይ ደብረብርሃን፣ መካነሰላም፣ እብናት፣ መቄት፣ መርጦለማርያም፣ ደባርቅ፣ ዳባት፣ ደሃና እና ሰሃላ ቦታዎች ላይ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎችን እያደረሱ መሆኑንም ገልጸዋል ዳይሬክተሩ፡፡