የምዕራባውያን የረዥም ርቀት የጦር መሳሪያዎች ሩሲያን አያስቆሙም -የክሬምሊን ቃል አቀባይ
ሩሲያ፤ የምዕራባውያን ድጋፍ ውጥረቱን ያባብሰው ይሆናል እንጅ፤ የጦርነቱን ሂደት አይለውጥም ብላለች
ዩክሬን ምዕራባውያን ተጨማሪ ወታደራዊ መሳሪያዎች እንዲያስታጥቋት ጠይቃለች
የሩሲያን ወታደራዊ ዘመቻ ለመቀልበስ ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን ምዕራባውያን ተጨማሪ ወታደራዊ መሳሪያዎች እንዲያስታጥቋት ጠይቃለች፡፡
ጥያቄውን ተከትሎ አሜሪካ 31 አብራም የተሰኙ ዘመናዊ ታንኮች እንዲሁም ጀርመን 14 ሊዮፓርድ የውጊያ ታንኮች እንደሚሰጡ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ዩክሬን በቅርቡ ባቀረበቸው የላቁ የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ ዙሪያ ከፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር እንደሚወያዩ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ የዩክሬን ጦርነት በማባበስ ምዕራባውያንን ተጠያቂ የምታደርገው ሩሲያ በቃል አቀባይዋ በኩል በሰጠችው መግለጫ፤ በጦር መሳሪያ ሚለውጥ እውነታ የለም ብላለች፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያቀርቧቸው የየረዥም ርቀት የጦር መሳሪያዎች የሩሲያ ወታደራዊ ዓላማ ሊያስቆሙ አይችሉም ብለዋል፡፡
"ይህ ውጥረቱን ያባብሰው ይሆናል እንጅ፤ የጦርነቱን ሂደት አይለውጥም" ሲሉም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
ፔስኮቭ ምላሹን የሰጡት ዋሽንግተን እስከ 150 ኪሎ ሜትር (93 ማይል) ሊምዘገዘጉ የሚችሉ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን ለመስጠት ማቀዷን ያልተረጋገጡ ዘገባዎች እየወጡ ከመሆነቻው ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው፡፡
በርካታ ክስተቶችን እያስተናገደ ሁለት አመት ገደማ ያስቆጠረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ወደ ኒውክሌር ግጭት እንዳያመራ ተሰግቷል፡፡
በዩክሬን ምድር ያለውን ውጥረት ያሰጋቸው የሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ወደ ኒውክሌር ጦርነት እየወሰደ ያለውን ሁኔታ እንዲያቆሙ በቅርቡ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡
የሀገራቱ መሪዎች "የኒውክሌር ሰዓቱን እንዲያቆሙ" የጠየቁት የቀድሞ የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የፑቲን የቅርብ ሰው እንደሆኑ የሚነግርላቸው ሜድቬዴቭ፤ የምጽአት ቀን ሊመጣ “ የኒውክሌር እኩለ ሌሊት” ላይ ነን ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡