በአማራና ኦሮሚያ ክልል ያሉ ግጭቶች በፖለቲካዊ ውይይትና በሰላማዊና መንገድ እንዲፈታ አሜሪካ ጠየቀች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተወያይተዋል
ብሊንከን በኢትዮጵያ እውነተኛ፣ ተአማኒና አካታች የሽግግር የፍትህ ሂደት ለማስፈን እየተሰራ ያለውን ስራ አድንቀዋል
በአማራና ኦሮሚያ ክልለ ያሉ ግጭቶች በሰላማዊና ፖለቲካዊ ውይይት እንዲፈታ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስገነዘቡ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በተናንትናው እለት ምሽት በስልክ መወያየታቸውን አስታውቀዋል
አንቶኒ ብሊንከን በኤክስ በቀድሞ ትዊተር ማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ችግሮች እንዲሁም የአንድነቷ የተጠበቀ፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያ የጋራ ግብ ላይ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ አንቶኒ ብሊንከን በውይይቱ ወቅት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ያለው ግጭት እንደሚያሳስባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢ መግለጻቸውን አስታውቋል።
በሁለቱ ክልሎች ያሉ የፀጥታ ችግሮች በፖለቲካዊ ውይይት እና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ አኳሃን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሰብአዊ እርዳታዎች ዳግም መጀመሩን ተከትሎ እየተሸሻሉ ባሉ የሰብዓዊ አቅርቦት ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።
በኢትዮጵያ እውነተኛ፣ ተአማኒና አካታች የሽግግር የፍትህ ሂደት ለማስፈን እየተሰራ ያለውን ስራም በአዎንታ እንደሚቀበሉትም አስታውቀዋል።